ለነጻነት ትግሉ እንቅፋት አንሁን ግርማ ቢረጋ

ሁሌም ግርም የሚለኝ በታሪክም እንዳየነው አምባገነኖች የሰፊውን ህዝብ እንቅስቃሴ በኃይል ለማፈን በመጨረሻው ሰዓት ካለፉት ከመማር ይልቅ ወደባሰ ጭፍጨፋና ህዝብን እርስ በእርስ ለማባላት የሚያደርጉት ያልሞት ባይ ተጋዳይነት የሚመስል ከሰው ልጅ አብራክ የተፈጠረ ፍጡር ሊያደርገው የማይገባ የእንስሳ ስራ በመስራት እድሜያቸውን የሚያራዝም እየመሰላቸው ከራሳቸው ባለፈ ከቤተሰባቸው የሚተርፍ ሰይጣናዊ ስራ ሆን ብለው መስራታቸው ራሱ ሰፊው ሕዝብ ወደማይቀረው ነፃነት የመጓዙ ምክንያትን በበለጠ የሚያጠናክረው እንጂ  የሚያስቆመው ሊሆን እንደማይችል አምባገነኖች ማሰብ ያለመቻላቸው ነው ። ለነገሩ በሃገራችን እየሆነ ላለው ለዚህ ሁሉ የወያኔ እብጠትና ማን አለኝብኝነት የሁላችንም ቸልተኝነት ውጤት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር  የለውም ምክንያቱም በተናጠል ሲገሉንና ሲቀጠቅጡን ያንዱ ህመም ሳይሰማን በመቅረቱና እነሱ በቀደዱልን መንገድ ብቻ በመሄድ አሁን ላለው ህብረተሰባችን የዘቀጠ ህይወትና የሃገራችን እንደ ሃገር የመቀጠል አደጋ የኛ ቸልተኝነት መብዛቱ እንደሆነ ልንክደው አንችልም። በተለያየ ግዜ ጥቂቶች ስለሃገራቸው ነፃነት ቤተሰባቸውን ጥለው ለማይቀረው ፍልሚያ መስዋዕትነት ሲከፍሉ አብዛኞቻችን ግን እነሱ የሚያመጡልንን ነፃነት ቁጭ ብለን የምንጠብቅ ግዑዝ ሆነናል ወይም ደግሞ በትናንሽ ጠባብ ቀዳዳዎች ውስጥ እራሳችንን ወትፈን መፈናፈኛ
ያጣ ነገር ግን የገባንበት ውታፍ ስህተት መሆንን ለመቀበል ወይም ከስህተታችን ለመማር ዝግጁ ባለመሆን እንዲሁም ይቅርታን መጠየቅ ከባድ ዳገት ሆኖብን በዘር ድሪቶ ተተብትበን ጥላቻን ለመስበክ ግን አፋችንን የምንከፍት ባዶዎች ሆነናል። በርግጥ ወያኔዎች የሸረቡልን ሴራ ቀላል አይደለም ነገር ግን በንፁህ ህሊና እንደሰው ልጅ ማሰብ ከቻልንና ራስ ወዳድነታችንን ገለል አድርገን እንደ አንድ ማሰብ የሚችል ፍጡር በዙሪያችንን እየተደረገ ያለውን በማስተዋል ሌሎች ስለሃገራቸው ምን እያደረጉ እንደሆነ ብቻ በመገንዘብ ከእኔነት ወጥተን ቀደም አባቶቻችን በኩራት ያስረከቡንን ኢትዮጵያ የተባለች ሃገር በታሪኳ ቀደም ብላ የፊት መሪ የነበረች ሃገራችንን
የማዳንም ሆነ የማስቀጠል ሃላፊነት የውዴታ ግዴታችንን ለመወጣት በተለያየ አቅጣጫ በሚደረጉ ተሳትፎዎች የአቅማችንን በማድረግ ከህሊና ወቀሳና አንካሳነት ልንድን የምንችልበት አጋጣሚ በሁሉም አቅጣጫዎች ስላሉ ትብብራችንን ኢትዮጵያዊነት ላይ ባተኮረ መልኩ መሳተፍ የሚጠበቅብን ሰዓት ላይ በመሆናችን ትብብራችንን ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ደርሰናል ። መወያየትና መቻቻልን አንድነትን በማስቀደም መድረስ የሚገባን ቦታ የመድረሳችን አቅም ምን እንደሆነ ለዘመኑ ጥጋበኞች ለማሳየት
ኢትዮጵያዬ ብለን እንነሳ።
ሞት ለዘረኞች እና ለነፃነት ትግሉ እንቅፋቶች!!!
ስቶክሆልም /ስዊድን

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *