ኦህዴድ የህወሃትን ህልውና ታዳጊ ወይንስ እራሱን አመንዳጊ?

የኢህአዴግ ሞተርና አስኳል የሆነው ህወሃት በሕዝባዊው ትግል ማእበል ከግራና ቀኝ እየተላተመ በውስጣዊ መሰነጣጠቅ ላይ ባለበት ወቅት የአብራኩ
ክፋይ በሆነው በኦህዴድ በኩል ለየት ያለ አካሄድ መታየት ከጀመረ ስንበትበት ብሏል።
ይህን ኦህዴድ መራሹን አዲስ አካሄድ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ እይታ በማየት ሲከፋፈሉ የተስተዋለ ቢሆንም በተለይም በዲያስፖራ ያለውን ማህበረሰብ
ከመከፋፈልም አልፎ ግራ ሲያጋባና ሲያምታታም ተስተውሏል።
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በ26 የኢህአዴግ አገዛዝ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም የኢህአዴግ አባል ድርጅትም ሆነ በኢህአዴግ መራሹ የፌዴራል
መንግስትና ህወሃትም ተገልጾ በማይታወቅበት ደረጃና አገላለጽ ኦህዴድ በአቶ ለማ መገርሳ ገላጭነት ኢትዮጵያዊነትን ይዞ መነሳቱ ብዙዎችን አስደስቶ
ያስፈነደቀውን ያህል ሌሎችንም አስደንግጦ አንገት ያስደፋና ብሎም አዲስ የጥቃት ፍላጻን ያስወነጨፈ ሆኖ ታይታል።
የአቶ ለማ መገርሳን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ማእከሉ ያደረገውን እንቅስቃሴ የህወሃት እራሱን ማዳኛ የእጃዙር ሕዝብ ማታለያና ሕዝባዊውን ትግል
መጥለፊያ እርምጃ በማለት ከማጣጣልም አልፈው ሀሳቡን ወደ ማጥቃት ደረጃ የተሻጋገሩ ወገኖች ቁጥር ቀላል ያልመሆኑን ያህል ግዜ ሰጥተን ልናየው
ይገባል በሚል ከመደገፍና ከመቃወምም ተግባር ተቆጥበው ክርክሩን በአንክሮ እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ሲታዪ በሌላ በኩል ደግሞ የአቶ ለማ
መገርሳን እርምጃ የኢትዮጵያ ትንሳኤ እስከማለት ደርሰው በፍጥነት በድጋፍ የተቃላቀሉ ወገኖችንም ለማየት ችለናል።
በእርግጥ የአቶ ለማ መገርሳና በድርጅታቸው ኦህዴድ እየተሰበከ ያለው ኢትዮጵያዊነት ህወሃትን የማዳኛ ወጥመድ የሆነ ሴራ ነውን ወይንስ የኦህዴድ
እራሱን ማዳኛና እራሱን መመንደጊያ አዲስ ራእይ ነው ብለን ልንጠይቅና ብሎም መልሱን እንድናገኝ ፍለጋ ላይ እንድንሰማራ አድርጎናል።
ኦህዴድና ህወሃት ተናንቀዋል ወይንስ ተሞዳምደውብናል? የነጻነት ሃይሎች ትግልና የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያደርገው ወደ ሁለንተናዊ የነጻነት ጎዳና ጉዞ
ላይ የአቶ ለማ መገርሳ መራሹ የኦህዴድ እንቅስቃሴ ሚና በአፍራሽ መልኩ ነው የሚጫወተው ወይንስ በደጋፊነት ሁኔታ ነው ሊገለጽ የሚችለው?
ለመሆኑ የኦህዴድና ህወሃት ወቅታዊ ሁኔታን በጌታና ሎሌ መካከል ያለ ግንኙነት ወይስ አንደኛው ሌላኛውን ውጦና ሰልቅጦ ለማለፍ የሚደረግ
የህልውና ግብግብ ላይ ያለ ግንኙነት ነው ያላቸው?ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ ፍለጋ በምናደርገው ጥረት ውጤቱ አጠቃላይ ብዣታውን የሚያጠራ
መልስ ያስገኛል በሚል እምነትና ጽሁፉ ተጠናቅሮ ቀርባልና ለጥቀን እንየው።
**   የኦህዴድና ህወሃት ትንቅንቅ እውነት ነው ውሸት?
ኦሮሞ ሲተርት “ደምቢን ቶኮን ቡላ ጄቴ ሁንዴ ታቲ” ይላል። ተቀራራቢ የአማርኛ ትርጋሜውም የተቀጽላ ዛፍ በበቀለችበት ዛፍ ላይ እድሜዋን
እንደምትገፋ እያመነች ድንገት ተሸካሚዋን ግንድ ውጣ እራሳ ግንድ ሆነች እንደማለት ነው። በህወሃት መዳፍ ተጠፍጥፎ የተፈጠረውና የህወሃት
ተቀጽላ የነበረው ኦህዴድ በእርግጥ እንደ ተቀጽላዋ ዛፍ የፈጣሪውን ህወሃት ድርጅታዊ አቃምና ተክለ ቁመና ውጦ እራሱን ችሎ እየቆመ ነው?
**   በኦህዴድ ከተወሰዱ ወሳኝ ተግባራት ውስጥ ጥቂቶችን ለአብነት እንግለጽ-
**    ባለፈው ሳምንት በፌዴራሉ የደህንነት ቢሮ ታውጆ የነበረውና በኦሮሚያ ብቻ የኮማንድ ፖስት
መቃቃምን የሚያዘውን ትእዛዝ የኦሮሚያ ክልል ደህንነት ቢሮና ፖሊስ መምሪያ “እኛ
የምንታዘዘው በኦሮሚያ ክልል መንግስት እንጂ በእናንተ አይደለም”በማለት እንቢ ማለታቸው።
 ኦህዴድ የህወሃትን ህልውና ታዳጊ ወይንስ እራሱን አመንዳጊ?
አዲሱን የኦህዴድ እርምጃና እንቅስቃሴን ህወሃት ከተዘፈቀበት ህልውናውን ተግደርዳሪ ችግር መወጣጫነት ተመርጦ በህወሃት ትእዛዝና ቁጥጥር ስር
እየተካሄደ ያለ ማጭበርበሪያ እያሉ ድርጊቱን የሚያጣጥሉ ወገኖችም በርክተው ሲደመጡ ተስተውላል።
የኦህዴድን እርምጃ በጥርጣሬ ከማየትም አልፈው ህወሃት ህልውናውን ለመታደግ የራሱን ተፈጣሪን ድርጅት እየተጠቀመበት ነው የሚሉ ሲሆን
**የኦህዴድ አመራርን ከተለመደው የህወሃት መራጭነትና አጽዳቂነት ውጪ በራሱ ኦህዴድ
ፍላጎትና መራጫነት ብቻ መምረጣቸው።
**     በኢሉባቦር ጥቃት እጁ ያለበትን የህወሃት ተወካይ ሃይሌ ኪሮስን ለማስለቀቅ የተጋዘውን  መከላከያ ሰራዊት ማረፊያ ስፍራ ከመንፈግ ጨምሮ በአጠቃላይ እንቅስቃሴውን ገድበው ታሳሪውን ለመፍታት አለመፈለጋቸው
**    በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች በህወሃቱ ደህንነቱ ሹም የሚፈጸሙትን ወንጅሎች በይፋ ማጋለጥ
**     በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በተለይም በሻሸመኔ፣ቦኩና ሌሎች ከተሞች ሰላማዊ ስልፈኞችን  የገደሉ መከላከያ አባላትን ማሰር
**      የኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ እንዳይወስድ ትእዛዝ ማስተላለፍ
**    በኦሮሚያ ውስጥ በኮንትሮባንድ፣በኢንቨስትመት ስም መሬትና የማእድን ስፍራ በተቆጣጠሩት  የህወሃት ባለሀብቶች ላይ ግልጽ እርምጃ መውሰድ
**    በሕገ-መንግስቱ ላይ የሰፈረውን የክልሎችን ስልጣን ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም መንቀሳቀስ
**   በአማራና ኦሮሞ መካከል ለ26ት ዓመታት ሲገነባ የነበረውን የልዩነት ግንብን አፍርሶ መሰረት ያለውና አንድነትን ያጠናከረ አዲስ ፈርቀዳጅ ግንኙነትን መመስረት እና የመሳሰሉትን መጥቀስ  የተቻለ ሲሆን በአንጻሩም ድርጅቱ በክልሉ ውስጥ ያለአግባብ ታስረው እየተሰቃዩ ያሉትን  የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት አለመቻል፣በምስራቅ የተፈናቀሉትን መብት ማስከበር አለመቻልና ዛሬም ጭምር በፌዴራሉ የሚገደሉ ኦሮሞዎችን መከላከል አለመቻሉ ድርጅቱ ዛሬም በህወሃት
መዘውር የሚሸከረከርና የራሱም ሉዓላዊ ህልውና የሌለው ተቀጽላ ሃይል ነው የሚሉ ወገኖች
አሉ።
               ኦህዴድ የህወሃትን ህልውና ታዳጊ ወይንስ እራሱን አመንዳጊ?
በተለይም በሻእቢያ ተማርኮ በስጦታ ለህወሃት የተሰጠው የአባዱላ ገመዳ ከፓርላማ አፈጉባኤነቱ ለቆ በድርጅቱ ኦህዴድ ውስጥ ሆኖ በህወሃት ላይ
ጀርባ መስጠቱን የህወሃት ስላቅ ሲሉ ይገልጻሉ።
እነዚህ ወገኖች በህወሃት ተጠፍጥፎ የተፈጠረውና በህወሃት ልብና ሳንባ የሚንቀሳቀሰው ኦህዴድ በምንም አይነት ተዓምር የራሱ ህልውና ኖሮት
ከህወሃት እቅድና ፕላን ፍላጎትና ፈቃጂነት ውጪ ውልፍት የሚልበት አንዳችም አቅምና ብቃት የለውም በማለት አጠቃላይ አዲሱን የኦህዴድ
እንቅስቃሴ ባለቤት ህወሃትን በማድረግ ሲያጣጥሉና ሲነቅፉ ታይተዋል።
የእነዚህ ወገኖችን መከራከሪያ ነጥቦችን አሳማኝነት ከግንዛቤ ውስጥ ሳላወጣ በአንጻሩም የተቀጽላው ኦህዴድ ወቅታዊ እንቅስቃሴና አቋም እውነተኛ
መንፈስ ከፈጣሪው ህወሃት ጋር ግብግብ እያደረገ ስለመሆኑ ሊያሳየን በሚችለው ነጥቦች ዙሪያ በማተኮር ሁኔታው የህወሃት የእጅ አዙር እርምጃ ብቻ
ሳይሆን የራሱ የኦህዴድ እውነተኛ የዓመጽ እርምጃ መሆኑን የሚያሳዩንን ገጽታ ክፍል ለማሳየት እፈልጋለሁ።
የደርግ ሰራዊት ምርኮኛ በሆኑ ስብስቦች ደራ ላይ በ1982ዓ.ም በህወሃት የተቋቋመው ኦህዴድ ከ28 ዓመታት የታዛዥነት ተግባሩ ወጥቶ እራሱን
የቻለና በፈጠረው ህወሃት ላይ ማመጽ የሚችልበት አቅምና ብቃት ከሚገባው በላይ እንዳለውና ሊኖረውም እንደሚችል ተፈጥሮአዊ ሂደቱ እንድናውቅ
ያስገድደናል።
ድርጅቱ   [ኦህዴድ ማለቴ ነው]ከህወሃት ጋር እያደረገ ያለው ግብግብ በትክክል ለራሱ ህልውና ሲል እያደረገ ያለ እውነተኛ ትንቅንቅ መሆኑን
ከሚያስረዳን ተግባራዊ እርምጃዎች ሌላ በተጨማሪም የተቀጽላ ድርጅቶች ተፈጥሮአዊ የእድገት ደረጃ ድርጅቱ ጥገኛ ሆኖ ከተፈጠረበት ሃይልን
ተጠቅሞ የራሱን ግለ ህልውና ከፈጠረ በሃላ እራሱን ችሎ የሚወጣበትና በጥገኝነት ፈጥሮ ያሳደገውን ሃይል ሰልቅጦ የመውጣት ሂደትንም ያካተተ
ሁኔታ መኖሩን ልናስታውስ ይገባል።
በተማሪና አስተማሪ መካከል ያለው ግንኙነት መጨረሻ ድምዳሜው በተማሪው አስተማሪውን በልጦና መምህሩን አስተማሪ ሆኖ መገኘት እንደሆነ
ይታወቃል።
ማንም ተማሪ እድሜ ልኩን የመምህሩ ተማሪ ሆኖ እንደማይቀር ሁሉ ማንኛውም ተገዢ፣ሎሌና ታዛዥ አገልጋይም እድሜ ልኩን የጌታው ታማኝ ሎሌ
ሆኖ እንደማይጨርስ የተፈጥሮ እድገት በግልጽ ያስተምረናል።
የኦህዴድ በህወሃት ተጠፍጥፎ መፈጠር፣የምርኮኛው የአባዱላ በወያኔ ምህረትና ፍቃድ ከምርኮኝነት ወደ ኦህዴድ መስራችነት፣መሪነት ብሎም ወደ
ጄኔራልነት ለጥቆም የኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነትና አፈጉባኤነት መሸጋገርን በመንተራስ ድርጅቱንና ሰውዪውን የእድሜ ልክ የህወሃት ታዛዥ ሎሌ አድርጎ
መፈረጅ ኢራሽናል የሆነና ሎጂካል ያልሆነ መሆኑን ነው የምናየው።
“ደምቢን ቶኮን ቡላ ጀቴ፣ ሁኔዴ ታቲ”የሚለው የኦሮሞ አባባል ተቀጽላ ስር በበቀለችበት ግንድ ላይ አንድና ጥገኛ ሆኜ እኖራለሁ እያለች መጨረሻ
ላይ ግን እራሳ ግንድ ሆና አረፈች የሚለው የተቀጽላዎች ተፈጥሮዓዊ እድገትን ያመላክታል።
ተቀጽላ ተክሎች በዋርካ ወይም ዝግባ ግንድ ላይ በመብቀል ይታወቃሉ። በግንዱ ላይ ጥገኛ ሆነው እየተሻሙ ካደጉ በሃላ ስራቸውን እያሳደጉና
የመሬቱን አፈር መንካት ሲጀምሩ በጥገኝነት ከተፈጠሩበት ትልቁ የዋርካ ወይም ዝግባ ግንድ ጋር ተግደርዳሪ እድገት ሲፈጥሩ ይታያሉ።
ስራቸውን ይበልጥ ወደ አፈሩ ውስጥ በጥልቅ መስደድ በቻሉ መጠን የተቀጽላዎቹ ግንድና ቅርንጫፎች እያደገ፣እየገዘፈና እየተንሰራፋ በመሄድ
በመጨራሻም በጥገኝነት የተፈጠሩበትን ዋርካ/ዝግባ አድርቀው በስሩ ይተኩና እራሳቸውን የቻሉ ዛፎች ይሆናሉ ወይም ከተጠጉበት ግንድ ተነጥለው
የራሳቸውን ግንድ በመፍጠር ከዋርካውና/ዝግባው ጎን የራሳቸውን መሬት የቆነጠጠ የዛፍ ግንድ ሆነው ቀሪውን ጊዜያቸውን ይኖራሉ።
የኦህዴድ ህልውና ግንድ በሆነው ህወሃት ላይ እንደተፈጠረ እናውቃለን። በህወሃት ግንድነት ላይ የተፈጠረው ኦህዴድ የራሱን ህልውና እውን
ለማድረግ ለተቀጽላዋ ዛፍ አፈር/መሬት የሚያስፈልገውን ያህል ለዚህ ድርጅትም መሬትና አፈር የሚሆነው ህዝብ እንደሚያስፈልገው እናያለን።
ህወሃት ግንዱ ሲሆን ሕዝብ ደግሞ መሬት/አፈር መሆኑን እንረዳለን። ዛሬ የኦህዴድ የእድገት ደረጃ በአስጠጊው ህወሃት ግንድ ላይ ጥገኝነት ተላቆ
ኦህዴድ የህወሃትን ህልውና ታዳጊ ወይንስ እራሱን አመንዳጊ?
የህልውናውን መሰረት በሆነው ሕዝብ ላይ ያደረገበት ደረጃ ላይ እንዳለ የተፈጥሮ እድገቱና ሂደት እያሳየን እንዳለ መረዳት እንችላለን።
ኦህዴድ ከእንግዲህ በኋላ ያለውን ግዜ በህልውናው ለመቀጠል የሚቻለው እራሱን በሕዝብ/አፈርና መሬት/ ላይ መሰረት አድርጎ ካልሆነ በስተቀር
ጥገኛ በሆነበት ህወሃት/ያበቀለውና ያሳደገው ግንድ/ላይ አድርጌ እቀጥላለሁ ካለ ሁለቱም ጠፊዎች ሲሆኑ እራሱን ከነጠለና የህልውና መሰረቱን
በሕዝብ ላይ ካደረገ ግን በህወሃት ምትክ እራሱን ተክቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ አድጎና ገዝፎ የሚታይ ድርጅታዊ ተክል ቁመናና ይዘት ይዞ የሚወጣ
ሃይል የመሆን እድል እንዳለው ነው መረዳት የሚቻለው።
ይህ አዲሱ ሃይል ለኦሮሞ ህዝብ እና ብሎም ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል ወይ ? ድርጅቱ የህወሃትን የበላይነት አምክኖ
ቢወጣ ለሀገሪቷና እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ትግል የሚያመጣው ለውጥና የሚጫወተው ሚናስ ምንድነው ? የድርጅቱ ተሳትፎና ሚና በእነዚህ
ነጥቦች ላይ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎችን ለመመለስ እራሱን የቻለ ማብራሪያ የሚያስፈልገው በመሆኑ በቀጣይ ጽሁፌ
እመለስበታለሁ።
በእያንዳንዱ ገዢ ሃይል ውስጥ በማህበረስቡ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ሃይል ይጸነሳል የሚለው የሌኒን አባባል ኦህዴድ በህወሃት ውስጥ ተጽንሶ ያለና
አሁን ልወለድ እያለ ያለ ሃይል እንደሆነ ይታያኛል።ከህወሃት ታዛዥነት ነጻ የሚሆነው ኦህዴድ የለውጥ ሓዋሪያ ለመሆን የማይቻለው ተግባር እንደሆነ
ብንገምት እንኳን ለለውጥ የሚኖረውን አስተዋጽኦ ግን ልንክደው አይቻለንም።
የድርጅቱ ህልውናም ከእንግዲህ በህወሃት ልጓም በኦሮሚያ ግዛት ብቻ የሚጋልብ የህወሃት ፈረስነቱ አክትሞ በኢትዮጵያ ደረጃ እራሱ ጋላቢ ለመሆን
በሚያስችለው ድርጅታዊ እድገት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይታየኛል። ድርጅቱ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ በእርግጥ እንደዘገየ ባምንም እድሜ ልኩን
የህወሃት ፈረስ ሆኖ በሎሌነት ይዘልቃል የሚለውን አመለካከት ግን እኔም እድሜ ልኬን የምመራበት እንዳልሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ።
`
አዲሱ የአቶ ለማ መገርሳ መራሹ ኦህዴድ አካሄድ የህወሃትን ህልውና ለመታደግ ብሎ እየተወነ ያለ ቲያትር ሳይሆን የራሱን ህልውና ለመመንደግ ሲል
ከህወሃት ጋር ግብግብና ትንቅንቅ እያደረገ ነው የሚለውን አባባል ይበልጥ የምስማማበትና የድርጅቱን ወቅታዊ ሁኔታ የምገልጽበት ቢሆንም ይህ
የለውጥ ንቅናቄ ግን እየተካሄደ ላለው ለሁለንተናዊ የነጻነት ትግል ወሳኝ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል እንጂ በራሱ ብቻ ግብ ሆኖ የምንፈልገውን
ሁለንተናዊ ነጻነት ያጎናጽፈናል ማለቴም እንዳልሆነ ከወዲሁ ለማስገንዘብ እወዳለሁ።
አዎን፣ አዲሱ የኦህዴድ አካሄድ እውነተኛና ከህወሃት የእጅ አዙር ትእዛዝና ፍላጎት ውጪ የሆነ አካሄድ ነው። በእርግጥም ለነጻነት ሃይሎችና
ለአጠቃላዩ ትግል ጠቃሚ ግብዓት በመሆን ትልቅ ሚናን መጫወት ይችላል። ግን ንቅናቄው በራሱ የህገራዊው ትግል ግብና መልስ ይሆናል ወይ
ብትሉ መልሱ የለም አይሆንም ነው።
የትግሉ ጎራ በዚህ ወሳኝ ወቅት ማድረግ የሚኖርበት ተግባሮች እና በኦህዴድ መራሹ እንቅስቃሴ ላይ የሚኖረን ሚና ብሎም መወጣት የሚገባን
ድርሻዎች ላይ የሚያጠነጥነውን ጽሁፌን በቀጣይ አቀርባለሁ።

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *