ጅጅጋ ካራማራ የሁላችንም ነዉ! (መቅዲ ዘ-ቨርጂንያ )

ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወደ 1 ሚልዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዉያን ኦሮሞዎች ተመልሰዉ መስፈር ያለባቸዉ እዛዉ ሀገራቸዉ ቄያቸዉ ላይ ነዉ። አስፈላጊዉ የመልሶ ማቋቋም ስራ ተሰርቶ ተወልደዉ ወደያደጉበት ቄያቸዉ በፍጥነት መመለስ አለባቸዉ። የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ጉዳዮች እስኪረጋጉ በመንግስት የታገዘ ህዝቡን የመጠበቅና የማረጋጋት ሃላፊነትና እድል ሊሰጣቸዉ ይገባል።

ሌሎችም ኢትዮጵያዉያን ከሶማሌ ክልል በተለያየ መንገድ እየተገደዱና እየተገፉ እንዲለቁ የሚደረገዉም አካሄድ በፍጥነት መቆም ይኖርበታል። ዛሬ የሶማሌ ክልል ተብሎ በክልል የታጠረዉ የኢትዮጵያ ክፍል ለኢትዮጵያዊያን ከደምና ከአጥንት ከመንፈስና ከስጋ ጋር የተዋሃደ ጥልቅ ትስስር ያለዉ ቦታ ነዉ። አባቶቻችን በከረን ያፈሰሱት ደም ከንቱ እንደቀረና ከረናዊያን ወንድሞቻችን በሊቢያ በባርነት እንዲሸጡ ያደረገዉ ጠባሳ ሳይሽር በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞና በሱማሌ ዜጎቻችን መሃከል ጠብ እየዘሩ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገዉን ሽረባ ከስሜትና ከግልፍተኝነት በወጣ መልኩ ተረጋግተን አስበን ማስተካከል ይኖርብናል።

ይህንን ሴራ በአስፈጻሚነት እንዲመሩ የተመደቡትን የሆድ አገልጋዮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ‘እንኳን አፈናቀላችሁልን’ በሚመስል መልኩ ዋንጫ በመሸለም ህዝቡን ደጋግሞ በማሳደድና በማስገደል የኦሮሞን ህዝብ በስሜትና በብስጭት ተነድቶ ህዝቤን በክልሌ አሰፍራለሁ የሚል የኩርፊያ እርምጃ እንዲወስድ ከጀርባ የሚገፋፉትን ሴራ ህዝቡና አመራሮቹ ጠንቅቀዉ ሊያዉቁ ይገባል። ዛሬ የሱማሌ ክልል ተብሎ የታጠረዉ ክልል የኦሮሞም የሌላዉም የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብትና ንብረት ነዉ።

ወያኔ የአስተዳደር ብስለትና ንቃት ስለሚያንሳቸዉ እንደ ልቤ የሀገርንና የህዝብን ሀብትና ንብረት ያለ ከልካይ እዘርፍበታለሁ ብሎ ያሰባቸዉን የሀገሪቱን ኮሪደሮች በሁሉም አቅጣጫ ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀስበትን ይህንን ከፍተኛ የሴራ አካሄድና የኮንትሮባንዲስቶች አሰራር ኢትዮጵያዉያን በንቃትና በብልሃት ሊከታተሉትና ሊያከሽፉት ይገባል። ቀደም ባሉት ግዜያት ከቤንሻንጉል ክልል በተደጋጋሚ በአማራ ህዝብ ላይ የተደረገዉ የግፍ ጭፍጨፋና ከየአከባቢዉ የማሳደድ ሂደት የዚህ ፕሮጀክት አካል መሆኑ መታወቅ አለበት።ከሀብት ዘረፋዉ ባሻገር ቁልፍ የሆኑ የሀገሪቱን መተናፈሻዎች የመቆጣጠሩ ዓላማ ግልጽ ነዉ።

መንግስት ለሀገር ደህንነት እነዚህን አከባቢዎች መቆጣጠር እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ቁመና ልክ መሰራት እንዳለበትና በሀገር ደህንነት ስም በዘረፋ የተሰማሩ ቡድኖች የሀገርን ድንበር ጭምር ያለ መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ እዉቅና ለጥቃቅን ሽርክናና ግዚያዊ ጥቅም አሳልፈዉ እየሰጡ በመሆኑ እነዚህ በሃገር ብሄራዊ ጥቅም ላይ እየታከኩ ሀገርን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት በፍጥነት በቃችሁ ሊባሉ ይገባል። ሌላዉም ኢትዮጵያዊና የየክልል አስተዳደር ባላስልጣናቱም ጭምር “ክልል ከልዬልሃለሁ ስለሌላዉ አከባቢ አያገባህም” የሚለዉን የወያኔ አደገኛ ትርክት ወደ ጎን ጥሎ ሁሉም የሀገሪቱ ጥግ የራሱ መሆኑን በመገንዘብ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

በማንኛዉም የሀገሪቱ ክፍሎች የህግ የበላይነት ሊሰፍንና በህዝብ ስም የሚፈጸመዉ የጅምላ ዘረፋ ከሀብት ባሻገር በህዝብ መሀከል ከፍተኛ የመከፋፈልና የመጠቃቃት መንፈስን እየፈጠረ ሀገሪቱን ወደ ማትወጣበት ማጥ እየከተተ ህዝቡንም ሀገርንም ከፍተኛ ኪሳራ ላይ እያደረሰ በመሆኑ እነዚህ ጥቂት የሀገር ሽፍቶች በሁሉም ርብርብ በህግ መዳኘት አለባቸዉ።መንግስትና የመከላከያ ሰራዊቱም በመንደር በተደራጁ የዛራፊ አካላት ሳይሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ቁመና ልክ መዋቀርና መመራት አለባቸዉ!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ ነገ ይገባዋል!!!

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *