የብዙሃኑ ፍላጐት-የጥቂቶቹ መብት! (ሰሎሞን ተሰማ ጂ) (ከአ/አ)

Published On: Thu, May 31st, 2012

 የሀገራችንና የህዝቧ እጣ-ፈንታ አስደማሚና አሳዛኝ ቀልዶችን በተጫነ የጊዜ በቅሎ፣ ፈረስ፣ ግመል፣ አይሱዙና ካሚዮን ታጭቆ ወደ ግንቦት ሲገሰግስ አይታያችሁም? “አስደማሚና አሳዛኝ ቀልዶች” ሁሉ አስቂኝ አለመሆናቸውንስ ልብ አላችሁ? “እንከን የለሽ!” ተብሎ ከነበረው የ1997 ምርጫ በኋላ፣ “ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዉና ተዓማኒነት!” ያለው ምርጫ-በምድር ኢትዮጵያ ይደረጋል የሚለውን ልፈፋ የሰማችሁ ጊዜ ምን ተሰምቷችሁ ነበር? ዛሬስ፣ ስለምርጫው ምን ዓይነት ግንዛቤ ጨበጣችሁ? አንባቢያንን፣ በጊዜ የጋማ ከብቶች ጀርባ፣ በአይሱዙና በካሚዮን መጫኛ ላይ አሳፍሬ ወደተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች እወስዳቸዋለሁ፡፡ ለምን ጥያቄዎችን እንዳዥጐደጐድኩባችሁም የኋላ-ኋላ ታጤኑታላችሁ፡፡ (በመጀመሪያ ግን አንድ ሁለት ቀልዶች እነሆ ልበላችሁ፡፡ ቀልዶቹን የነገረኝን የሀረሩን ቀልደኛ-ኢሳያስ “ታክሲን” አመስግኑልኝ”፡፡)

 ቀልድ አንድ
በ160 ብር የጡረታ ገቢ፣ አስራ ስድስት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት፣ አባባ አብዱሌ፣ በጣም የተለዩ ሰው ናቸው፡፡ ሚስታቸውንና ሰባት ልጆቻቸውን፣ እንዲሁም፣ ስምንት የልጅ ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩት፣ በ160 ብር የጡረታ አበል ገቢያቸው መሆኑን ሲያስቡት ይደመማሉ፡፡ ከእለታት አንድ ቀን ታዲያ፣ ከልጅ ልጆቻቸው አንዱ፣ ትንሹ ሙኒር መጥቶ፣ “ባባ-ባባ!” አላቸው፡፡ “አቤት!” አሉት-በፍቅር ስሜት፡፡ “እ…እኛ ትምህርት ቤት አንድ ጥቂት ብሮችን ብ…ዙ የሚያደርግ አስማተኛ መጥቷልና ገብቼ እንዳየው አምስት ብር ስጡኝ!” አላቸው፡፡ አባባ አብዱሌም፣ “ይልቅስ እኔን በነፃ አታየኝም፣ በመቶ ስልሳ ብር አስራ ስድስት ቤተሰብ የማስተዳድረውን ሚስኪኑን አስማተኛ!” አሉት፤… ይባላል፡፡
ዛሬ፤ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የሚነግረንን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ጥናት (National Conception) ሳይሆን፣ እንደ አባባ አብዱሌ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች አስደማሚ ቀልድ ስንሰማ፣ አሳዛኝ ብሔራዊ ስዕል ፊታችን ላይ ይደቀናል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በምግብ እህሎችና በዕለት የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማቆም የደፈረ የፖለቲካ አመራርም ሆነ መንግሥት በቁርጠኝነት ሲወስን አናይም፡፡ በነዳጅ ዋጋ፣ በትራንስፖርትና በኃይል አቅርቦቶች የአገልግሎት ሂሳብ ላይ ያለለው ጭማሪ፣ እንደ አባባ አብዱሌ ያሉትን ሰዎች ወደ ግማሽ የጐዳና ተዳዳሪነት (half-street off) ህይወት እየገፋቸው ነው፡፡
የዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያቶች በቅርቡ እንደተገነዘብኩት ከሆነ፣ ከሀገር ቤቱ ተጠቃሚ አፍና ጉሮሮ እየነጠቁ ወደ ውጭ የሚልኩት ወገኖች ናቸው፡፡ ወደ አውሮፖ በረራዎች ተስተጓጉለው በነበረበት ወቅት ኪሎ ሙዝ በሶስት ብር፣ ኪሎ ቲማቲምም በሁለት ብር ሂሳብ ገብይተናል፡፡ አንድዬ አሁንም ሌላ የእሳተ-ጐመራና የአየር መዛባት አያምጣባቸው እንጂ፣ የአውሮፖ ከርሳም ሸማቾች፣ በማን ምርትና አቅርቦት ላይ ጥገኛ እንደሆኑም ተገንዝበናል፡፡
አባባ አብዱሌና እርሳቸውን መሰሎች በአስማት ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ አባወራዎችና እማወራዎች፤ የኢህአዴግ ፈለጋቸውን ያህል የአየር ሰዓት ተሻምተው ቢጮሁ፣ ማንን እንደሚመርጡ ያውቃሉ፡፡ በእነርሱ ስር የሚተዳደሩትም ለመምረጥ ብቁ የሆኑት ዜጐችም ቢሆኑ፣ “የኢኮኖማ መረጋጋትንና ማህበራዊ ፍትህን ያሰፍናል” ብለው የሚያምኑበትን ፖርቲ እንደሚመርጡ ያውቁታል፡፡ ቀልድ ሁለት
አንድ አኪሩ የመጣለት አራጋው የተባለ ሰው፣ ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ አፍስሶ-አንድ የጭነት መኪና /ISUZU/ ገዛ፡፡ አውጥቶና አውርዶ “እራሴ ብነዳው ይሻለኛል!” ብሎ ወሰነ፡፡ ከዚያም፣ ከመኪናው የኋላ ተካፋች ብረት ላይ “ገብርኤል ተከተለኝ!” የሚል ፅሑፍ በትልቁ አፃፈበት፡፡ የጫነውንም ጭኖ-በፍጥነት ወደ ሀርት ሼክ በረረ፡፡ ድንገት ተገልብጦ፣ አራጋው ሆዬ ከሞት ለጥቂት አመለጠ፡፡ መኪናውንም አሳድሶ ሲያበቃ፣ ቆይ አሁን ደግሞ “ሚካኤል ተከተለኝ!” ብል ይሻላል ብሎ አሰበና-በትልቁ አፅፎ የመጀመሪያው ፁሑፍ ላይ ደረበበት፡፡ የጫነውን ጫት አጭቆ ወደ ጅጅጋ ሲከንፍ ሶስት ጊዜ ተገልብጦ-አራጋው ሆዬ ለጥቂት በህይወት ተረፈ፡፡ እንደተለመደው-መኪናውን አሳድሶ ሲያበቃ፣ “ማንም እንዳይከተለኝ!” የሚል ፁሑፍ አፅፎ-ወደ ደጋሃቡር መክነፍ ጀመረ፡፡ አሁን ግን ከወገብ በላይ-አከርካሪው ተሰብሮ-ሽባ መሆኑን ሀኪሙ አስረዳው፡፡ ወሬውን የሰሙ ሁሉ እየመጡም ያፅናኑት ጀመር፡፡ የንስሐ አባቱም፣ አባ ናሁሰናይ መጥተው፤ “ምነው ልጄ መገልበጥ አበዛህ?” ሲሉ አውራጣቱን ይዘው ጠየቁት፡፡ አቶ አራጋውም፣ “አባ፣ በመጀመሪያ ገብርኤል ተከተለኝ አልኩት-ሳይከተለኝ ቀርቶ ኖሮ፣ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ፣ ሚካኤል ተከተለኝ!” ብዬ ተማፅኜው ብሔድ እርሱም እንደጓደኛው ሳይከተለኝ ቀርቶ ኖሮ ሶስቴ ተገልብጬ ተረፍኩ፡፡ ከዚያ፣ ተናደድኩና “ማንም እንዳይከተለኝ!” ብዬ ብወጣ ይሄው ከወገብ በላይ ሽባ ልሆን ነው፡፡” አላቸው – ስብር ባለ ድምፅ፡፡ አባም፣ “እኔ እምልህ ልጄ፣ በሰዓት ስንት ኪሎ ሜትር ነበር የምትበረው?” ሲሉ ጠየቁት፡፡ አራጋውም፣ “መቶ ስልሳና መቶ ሰባ ኪሎ ማትር!” አላቸው ኮራ ብሎ፡፡ “አዬ ልጄ-መልአኩ ገብርኤልም ሆነ-ሊቀ መልዓኩ ሚካኤል ተከትለውህ ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ እንዴት ብለው ይድረሱብህ!” ሲሉ እቅጬን ነገሩት፤… ይባላል፡፡

 
የጊዜአችን አይሱዙም፣ እየገሰገሰ-አስደማሚ ቀልዶችንና አሳዛኝ ኩነቶችን ጭኖ እየተፈተለከ ነው፡፡ ይህ የዘመናችን አይሱዙ፣ እንኳን ለነቢያትና እንደኔ ላለው አምደኛ ቀርቶ፣ለመላእክትም ግምትና ክትትል በሚያዳግት ፍጥነት-የብርሃን ፍጥነት ወደፊት “ሽው-እልም!” እያለ ነው፡፡ የአቶ አራጋውን መሠል መሪውን የጨበጡ ሰዎች በሚመኙት ፍጥነትና ችኮላ-እየተምዘገዘገ፣ አደብ አጥቶ፣ ፀጋውንና ሰላሙን ለአደጋ አጋልጦ፣ ጤንነቱንና ህሊናውን ለገንዘብ፣ ለዝናና ለዝሙተኛ ሥልጣን ቋምጦ-ወደፊት እየፈረጠጠ ነው፡፡ ጥችሩ፣ የሀገርንና የህዝብን የወደፊት እጣ-ፈንታ የሚዘይረውን መሪ የሙጥኝ ብለው የጨበጡት ግለሰቦችና ቡድኖች ከእነርሱ ክብር የሀገርና የህዝብ ፍላጐት እንደሚበልጥ አለማወቃቸው ላይ ነው፡፡ ወይም፣ ሆን ብለው “ቸለል!” አርገውታል፡፡ ለገንዘብ፣ ለዝናና ለፖለቲካ ስልጣን መገስገስ የእነዚህ ጥቂት የፖርቲና የድርጅት ሹፌሮች መብት ቢሆንም ቅሉ፣ የብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጐትና ምኞት ግን፣ ሰላም-ነፃነት-ልማትና ብልፅግናን ከርቱዕ ፍትህ ጋር ነው፡፡ በቃ፤ “ገብርኤል-ተሻረ፣ ሚካኤል-ተሾመ!” የሚባለው የመንግስተ-ሥልጣን አታካሮ-ለብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ “የድህነት ቀንበሩን” አይፈታለትም፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ፣ ዛሬ ድህነትና ረሃብ፣ የWFP- (የአለም የምግብ ኘሮግራም ግምት ከሆነ) ከስምንት ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለምግብ ለስራ (safety net) ሲዳረግ፣ አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ገደማ የሚሆነውም ህዝብ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊነት የትጋለጠ ሆኑዋል። ይህም ቁጥር፣ ሰማንያ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ካላት ኢትዮጵያ፣ አንድ ስድስተኛ የሚሆነው ህዝቧ በረሃብ አለንጋ እየተሸነቆጠ መሆኑን ያሳያል፡፡ (እስቲ አንድ ግጥም ስለወቅቱ ሁናጤ ቢገልጥልኝ ልሞክር!)
(ግጥሙ ርዕስ የለውም!)
የፈሩትስ ነገር፣ መድረሱ አይቀርም፣
ምነው “ኡ-ኡ!” በዛ፣ እኛ አላማረንም፡፡
“ሰላም-ሰላም!” አሉ፣ በየሬዲዮው ላይ፣
“ዲሞክራሲም!” አሉ፣ ቴሌቪዥኑ ላይ፣
“ታማኒ ይሁን!” አሉ፣ በየጋዜጣው ላይ፣
እያለ እንደሌላ፣ እያዩት ባይታይ!
የፈሩትስ ነገር፣ መሆኑ አይቀርም፣
ምነው ሟርቱ በዛ፣ እኛ አላማረንም! …………………
ጉራፈርዳ አኩርፎ፣ ታየኝ ለንቦጩ፣
ጋምቤላ ላይ ሳይቀር፣ ታየኝ አገጩ፣
ዋልድባ ላይም፣ ይታያል ለንቦጩ፣
አሳሳ አወሊያ፣ ይታያል አገጩ፣
የችግሩስ ምንጩ፣ ዝምታው እርጩ። (ቸር ይግጠመን!)

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *