የ‹‹አራት ኪሎው›› እና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› ወግ

Tuesday, June 5, 2012
  • ሁሉም እንስሳት እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንሰሳት ከሌሎቹ ይበልጥ እኩል ናቸው

ተመስገን ደሳለኝ ሲሳይ አጌና በቅርቡ በመጀመሪያ በጀርመን፣ ቀጥሎ በአሜሪካን ሀገር ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› የሚል ርዕስ ያለው መፅሐፍ አሳትሟል። በእርግጥ መፅሐፉ እስከአሁን ሀገር ቤት መግባት አልቻለም (ምናልባት ወደፊትም ላይገባ ይችላል)
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ታሪክ የጎላ አሻራ ካላቸው ጥቂት ጉምቱ እና ትንታግ ጋዜጠኞች አንዱ ነው። ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ በድህረ ምርጫ 97 በተነሳው አለመግባባት ስራ እስካቆመበት ዕለት ድረስ ‹‹ኢትኦጵ›› እና ‹‹አባይ›› የተባሉ ጋዜጦችን በባለቤትነት ይመራ ነበር። በተለይ ኢትኦጵ ጋዜጣ በእጅጉ ተወዳጅ ከመሆኗም ባሻግር በስርጭትም ግንባር ቀደም እንደነበረች ይታወሳል። ጋዜጠኛ ሲሳይ ከቅንጅት መሪዎች ጋር አብሮ ታስሮ ነበር። የተለቀቀውም ልክ እንደእስክንድር ነጋ ፍርድ ቤቱ ‹‹ነፃ ነህ›› ብሎት ነው፡፡ ይህ አንድ እውነት ቢሆንም ብሮድካስት ኤጀንሲ የተባለ ‹‹ፍቃድ ሰጪ እና ፍቃድ ነሺ›› መስሪያ ቤት ወደ ፕሬሱ እንዳይመለስ በመከልከሉ ዛሬ በአሜሪካን ሀገር በስደት ይኖራል። ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› የሚል ርዕስ የሰጠውን መጽሐፉንም ያሳተመው በዛው በስደት አለም ነው። (በነገራችን ላይ ይህ ፅሑፍ የመፅሐፉ ዳሰሳ /Book review/ ባለመሆኑ ስለመፅሐፉ ይዘት፣ ጠንካራ እና ደካማ ጎን አንነጋገርም። የምንነጋገርበት አብይ ጉዳይ በመጽሐፉ ላይ ስለተገለፀው የፍትህ ስርዓቱ ሹቀት፣ የፀጥታ አስከባሪዎች ገለልተኛ ያለመሆን፣ ስለእስረኛ አያያዝ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ብቻ ነው።
ይህንን መንገድ የመረጥኩበት አንዱ ምክንያት የሚመለከተው ክፍል ቢያንስ በዋና ዋና ጉዳዮቹ ላይ መልስ ይሰጥበታል በሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከመጋረጃው ጀርባ ያለውን የኢህአዴግን ፖለቲካ ‹‹ፈገግ›› በሚያደርጉ ገጠመኞች ታጅበን ለማየት እንዲያስችለን ነው) በቅድሚያ ሲሳይ አጌና ይህንን መፅሐፍ ለምን እንዳዘጋጀ በመግቢያው ላይ ከገለፀው ጨርፈን እንይ፡- ‹‹…ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በዚሁ የፕሬስ ሥራ ሳቢያ ለ6ኛ ጊዜ መታሰሬ ነው። ይህንን እንደ ገድል ልዘክረው ያነሳሁት ሳይሆን፣ የነፃው ፕሬስ ባልደረቦች ‹ሕዝብና መንግስት በማጋጨት›፣ ‹ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት› እየተወነጀልን ስንታሰር ስንፈታ መኖራችንን በማስታወስ፤ በእስር ቤቱ ‹ደንበኝነቴ› የሰበሰብኳቸውን መረጃዎች በመጽሐፉ ውስጥ በየአጋጣሚው ስለሚነሳ ይህን በሰሚ ሰሚ የቃረምኩት ሳይሆን፣ ራሴ ያለፍኩበትና ከምንጩ በቀጥታ የተቀዳ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው። እርግጥ ነው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ከበደ፣ ጋዜጠኛ መኮንን ወርቁ፣ ጋዜጠኛ ታምሩ ተስፋዬ የተባሉ የነፃው ፕሬስ ባልደረቦች ራሳቸውን እስከማጥፋት የዘለቁበትን አስጨናቂ ሂደት ማለፋችንንም መግለፅ ራሱ ስለነፃው ፕሬስ ፈተና ብዙ ይናገራል። ከእነዚህ ሶስቱ ጋዜጠኞች አንዱ መኮንን ወርቁ በፖሊስ ያልተቋረጠ ክትትል በመማረርና በሌላ የፕሬስ ክስ ዋሱ የነበሩት ሰው በመታሰራቸው በሞቱ ነፃ ሊያወጣቸው በራሱ ላይ ዕርምጃ የወሰደ ሰማዕት ነው።›› የፈጣሪ ያለህ! ምን ያህል አስጨናቂ ጫና ቢሆን ነው ራስን እስከማጥፋት የሚያደርሰው? ይህ መጽሐፍ የሚያተኩረው በይበልጥ በድህረ ምርጫው ‹‹ጦስ-ጥንቡሳስ›› የቅንጅት መሪዎች ከያሉበት ጓዳ ጎድጓዳ ታድነው እንዴት እንደተያዙ፣ ቀጥሎም የእስር አያያዛቸው እና የፍርድ ቤት ውሎአቸው ምን ይመስል እንደነበረ ነው። በዚህ አጋጣሚም ነው በሀገራችን የፍትህ ስርዓት ላይ ስጋት እንዲገባን የሚያደርጉ አስደንጋጭ እና በቁጣ የሚያነዱ ክስተቶችን ከመፅሀፉ ላይ ያገኘሁት። ያችን ሰዓት ‹‹መጨረሻው ሲጀመር›› በሚል ርዕስ ፖለቲከኞቹ እና ጋዜጠኞቹ እንዴት ታድነው እንደተያዙ ተዘርዝሯል። ‹‹ያች ሰዓት›› (ጥቅምት 22/1998 ከቀኑ 10 ሰዓት በኋላ ጀምሮ ነው) የደህንነት ሀይሎች ለወራት ሲከታተሉና ሲያዋክቡ የቆዩትን ታሳሪዎች አሳደው መያዝ የጀመሩባት። ዕለቷ በአዲስ አበባ ዋና ዋና ቦታዎች ‹‹በምርጫው ኢህአዴግ አጭበርብሮአል›› ያሉ ወጣቶች ዛሬም ድረስ ጥሪው ከማን እንደተላለፈ ተለይቶ ያልታወቀ ‹‹የመብት ጥያቄ››ን በማንገብ በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ከታጣቂዎች ጋር የተፋጠጡበት የጭንቅ እና የሰቆቃ ሰአት ናት -ያች ሰዓት። በእርግጥ ይህ መጽሐፍ ለጅምላ እስሩ የእለቱ ግጭት ብቻ ምክንያት እንዳልሆነ ይሞግታል። እንደ ምክንያት የሚያስቀምጠውም ቅንጅቱ መስከረም 22/1998ዓ.ም ‹‹ከቤት ውስጥ ያለመውጣት›› አድማ እንዲደረግ ያስተላለፈውን ጥሪ በዋዜማው በዲፕሎማቶች ጫና ከሰረዘው በኋላ፣ በእለቱ በታላቁ ቤተ-መንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ዲፕሎማቶቹ ባሉበት በተደረገ ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ‹‹ቤት የመቀመጥ ጥሪውን ባትሰርዙት ኖሮ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሰብስቤ ላስራችሁ ነበር›› ያሉትን በመጥቀስ ነው። እንግዲህ ምንም አይነት የጎዳና ላይ ነውጥ ሊቀሰቀስ የማይችል የትግል ጥሪ ያስተላለፉ ሰዎች ሊታሰሩ ተወስኖ ከሆነ ልክ በወሩ ‹‹ህገ መንግስቱን በኃይል ሊንዱ ነው›› ተብለው የታሰሩበትን መንግስታዊ ምክንያት ያፋልሰዋል ማለት ነው። (የመጽሐፉ ደራሲ ሊያስሩት ከመጡ የፀጥታ ሰራተኞች አምልጦ ለአንድ ወር ከተደበቀበት ተይዞ ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄድ ያጋጠመውን ፈገግ የሚያሰኝ ሁኔታ ደግሞ እንዲህ ሲል ይጨምርልናል፡- ‹‹…ሹፌሩ ከመስቀለኛው መንገድ በቀጥታወደ ግራ መታጠፍ ሲገባው ወደ ቀኝ ታጥፎ የአዲሱ ገበያን መንገድ ተያያዘው። በመገረም ወዴት እየወሰደን ነው? በማለት ከራሴ ጋር ስሟገት እንደገና ወደ ግራ ታጥፎ ቁልቁል የጊዮርጊስን መንገድ ያዘ፡፡ ወደ ማዕከላዊ ምርመራ ማስተባበሪያ ይገባል ብለን ስንጠበቅ ቁልቁል ሸመጠጠ። በመኪና ውስጥ ያጀቡን አራት መሳሪያ ያነገቱ ፖሊሶችና አንድ ከሹፌሩ ጎን የተቀመጠው ኃላፊያቸው እንዲሁም ሹፌሩ ማዕከላዊ ምርመራ የቱጋ እንደሆነ በትክክል እንደማያውቁ የተገነዘብኩት ይሄኔ ነበር። ግራ በመጋባት የትኛው ነበር እያሉ ሲጠያየቁ መኪናውን አዙረው እንዲመለሱ የነገርኳቸውና የምታሰርበትን ግቢ ያሳየኋቸው እኔው ራሴ ነበርኩ።›› መቼም ይህ በእጅጉ የሚደንቅ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ ፀጥታ አስከባሪዎች ‹‹ለፀጥታው አስጊ›› ያሏቸውን ሰዎች አድነው ከያዙ በኋላ የሚያስሩበትን ዋነኛ ቦታ አለማወቃቸው በወቅቱ ‹‹የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሰራዊት›› ጣልቃ ገብቶ ነበር እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናልና። እስር ቤቶቹ ጠዋት እና ማታ ወደ መፀዳጃ ቤት ብቻ መሄድ እንደሚቻል ፈቅዶ የቀረውን ሙሉ ሌሊት እና ሙሉ ቀን በተቆለፈ በር ውስጥ ከመገደቡ ውጭ የማዕከላዊ እስር ቤት ከሌሎቹ የሀገሪቱ እስር ቤቶች የተሻለ እንደሆነ ይነገራል። ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› መፅሐፍም ይህንን ያረጋግጣል። ከዚህ ውጭ የቃሊቲው ማረሚያ ቤት ‹‹የምድር ሲኦል›› ነው፡፡ የመጽሐፉ ትርክት ደግሞ እስር ቤቱን ከሲኦልም በላይ የከፋ አድርጎ ገልፆልን ሲያበቃ፣ ስቃዩን ይበልጥ በመከራ የተመረገ የሚያደርገው ማረሚያ ቤቱን የሚያስተዳድሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ለገዥው ፓርቲ የወገኑ መሆናቸው እንደሆነ ይገልፃል። ‹‹ፖሊስ ገለልተኛ ነው›› የሚባለውም በወረቀት እንጂ በተግባር በግልባጩ ነው ሲልም ያረዳናል። ወይም የምናውቀውን ሃቅ ያረጋግጥልናል። በእርግጥ ትርክቱ በደረቁ አይደለም። ምክንያታዊ ነው። ለምሳሌ ታህሳስ 26/1998 ዓ.ም. ጋዜጠኞቹ እና የጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቶቹ ባ
ለቤቶች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በመመካከር ሁሉም ‹‹ጥቁር ቲሸርት›› ለብሰው የህሊና እስረኞች እንደሆኑ ለማሳየት ጥረት አደረጉ። ሙከራቸውም ተሳክቶ ድርጊቱ የዜና ሽፋን አገኘ። ሆኖም ማረሚያ ቤቱ የእስረኞቹን ሻንጣ ፈትሾ ጥቁር ቲሸርት የተባለ እንዲወረስ ከማድረጉም በላይ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ከቤተሰብ፣ ለእስረኞቹ ጥቁር ቲሸርት እንዳይገባ ከልክሏል፡፡ ይህ አንዱ ማሳያ ነው። አፍንጫ ሲመታ… ሌላው ይቀጥላል። ‹‹በዚያ 250 ያህል ሰው በሚይዘው አዳራሽ ውስጥ ደስታ፣ መሐሪ፣ ለገሰ፣ አባስ፣ ኃይሉ የሚባሉ የአእምሮ በሽተኞች ያሉ ሲሆን፣ ጆንሰን የሚባለው ሱዳናዊ ወፈፌ ሲጨመር 6 የአእምሮ በሽተኞች ከእኛ ጋር ይኖራሉ።›› ይልና በሌላ ገፅ ላይ ደግሞ በትክክል ተቆጥረው ሃምሳ የሚሆኑ የሳምባ በሽተኞች በዚሁ ክፍል እንዲገቡ መደረጉ ለጤና አደገኛ በመሆኑ ለፍርድ ቤቱ እስከማመልከት ቢደረስም የተገኘ ለውጥ እንደሌለ ያትታል። እዚህ ላይ አጥንት ድረስ ሰርስሮ ከሚገባ ሀዘን ጋ የሚያላትመን መሀሪ እና አባስ፣ እንዲሁም አማርኛ መናገርም ሆነ ማንበብ የማይችለው ከቤንሻንጉል ስራ ፍለጋ የመጣው (ስሙ ያልተጠቀሰ) ታሳሪን ጨምሮ ሶስቱም የአእምሮ በሽተኛ የሆኑት ሚያዝያ 10 ቀን 1993 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተነሳው አመፅ ተይዘው ‹‹ህገ መንግስቱን በኃይል በመናድ እና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ውድመት በማስከተል›› የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ደንግጠው መሆኑ ነው። መሀሪ ስራ ፍለጋ ከጎንደር የመጣ ሲሆን፣ አባስ ደግሞ ጫማ በመጥረግ የሚተዳደር ሊስትሮ ነበር። ሲሳይ የቤንሻንጉሉ ወጣት አማርኛ አለመቻሉን ጠቅሶ እንዲህ ይላል ‹‹ከእነአባስ ጋር በምን ቋንቋ መክሮ በወንጀሉ ተባባሪ እንደሆነ የሚያውቀው ዐቃቢ ህግ ብቻ ነው›› የሀገራችንም ሆነ አለም አቀፍ ህጎች ስለእስረኛ አያያዝ ደንግገዋል። እናም በምንም መልኩ በትንፋሽ በሚተላለፍ በሽታ የተያዙ እና የሚያደርጉትን የማያውቁ የአእምሮ ህሙማን ከጤነኛ ጋር መታሰራቸው ለማንም ሰው አደገኛ መሆኑ አይጠፋውም። የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሀላፊዎችን ጨምሮ። መቼም ታሳሪዎቹ ‹‹ምርኮኛ›› ናቸው የሚል የለም። ለነገሩ ምርኮኛም ቢሆኑ በእንዲህ አይነት ሁኔታ እንዳይታሰሩ ህጉ በበቂ ሁኔታ ይከለክላል። የሲሳይ አጌና ‹‹ፖሊስ ገለልተኛ አይደለም›› መከራከሪያም ከብዙ ጥቂቱ ይህ ነው። በእርግጥ ይህ ጥያቄ የእኔም ነው። ፖሊስ ገለልተኛ ከሆነ ከገዥው ፓርቲ ጋር በሃሳብ የተኳረፈን እስረኛ ስለምን በእንዲህ አይነት አደገኛ ጥቃት ይበቀላል? መልስ የሚያስፈልገው ነው። ምናአልባትም የአንዱአለም አራጌን ከሌላ ክፍል ተቀይሮ በመጣ እስረኛ መደብደብ ከዚህ ጋር እያነፃፀርን አብዝተን ልንጠረጥር እንችላለን። አሊያ ህገ መንግስቱ የተናደው በታሳሪዎች ሳይሆን በአሳሪዎች ነው የሚለውን ዛሬም ድረስ በህይወት ያለን መከራከሪያ አጥብቀን እንድንይዝ እንገደዳለን። ማነው መንግስት? ሲሳይ አጌና ለመፅሐፉ ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› የሚል ርዕስ የሰጠው የቅንጅት መሪዎች ቃሊቲ በታሰሩበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ምዕራባውያን ባለስልጣናት በሙሉ በአራት ኪሎ ቤተመንግስት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ከተወያዩ በኋላ፣ በቀጥታ ወደ ቃሊቲም ሄደው ከታሳሪዎቹ ጋር መወያየታቸው የተለመደ ተግባር መሆኑን ያስተዋሉ የወህኒ ቤቱ እድምተኞች፣ የቅንጅት መሪዎችን ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› እያሉ መጥራታቸው መጽሐፉን በዚህ ርዕስ እንዲሰይም እንዳደረገው በተዋበው ብዕሩ ይተርካል። ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከአራት ኪሎ እና ከቃሊቲው መንግስት ጋር ተወያይተው ከተመለሱ ባለስልጣናት ውስጥ የአየርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የአየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሊቀመንበር፣ የአየርላንድ የፓርላማ ቡድን አባላት፣ በወቅቱ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሀላፊ ዶናልድ ያማማቶ (በኋላ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነዋል)፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር እና የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ዶናልድ ፔይን፣ ታዋቂው አሜሪካዊው ምሁር ዶናልድ ሌቪን፣ የአውሮፓ ህብረት የልማትና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሉዊ ሚሽል፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚስስ ሉዊስ ኦርበር፣ የሲፒጄ (CPJ) ሀላፊዎች… ሲሆኑ፤ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ የአለም የጋዜጠኞች ፌደሬሽን /IFJ/ እና የአለም የስራ ድርጅት /ILO/ ተወካዮች ደግሞ እስረኞቹን እንዳይጎበኙ ከተከለከሉት ውስጥ ይገኛሉ። በእርግጥም መንግስት ቀን እና ማታ ‹‹ህገ-ወጦች፣ ነውጠኞች፣ አድመኞች፣…›› በሚል ውግዘት በተጠመደበት በዛ ‹‹ክፉ ቀን›› እነዚህ ሁሉ ባለስልጣናት፣ ያውም አስፈሪ አንደሆነ የሚነገርለት ቃሊቲ እስር ቤት ድረስ ሄደው በሀገር ጉዳይ እና በመሳሰሉት ላይ መወያየታቸውን ስናስተውል ለእስረኞቹ የተሰጠው የዳቦ ስም በልክ የተሰፋ ይመስላል-እውነትም የቃሊቲው መንግስት። ስንት ግራም ማስረጃ? ሲሳይ በፍርድ ቤት በእሱ እና በፖለቲከኞቹ ላይ የቀረበው መረጃ የኮረኮሩትን ያህል ያሳቀው ይመስላል። የሳቁ መንስኤም ታሳሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሰዎቹ ህግ-ለመጣሳቸው፣ ወንጀል ለመፈፀማቸው ‹‹በቶን የሚቆጠር መረጃ አለን›› ማለታቸውን በችሎቱ ከቀረበው ማስረጃ ጋር አመዛዝኖ ነው። እኛም ወይ ለመሳቅ አሊያም ለማዘን ክሱን እና ማስረጃውን ነጣጥለን እንየው። ክሱ ይቅደም፡- ‹‹ተከሳሾቹ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ በተሰኘ ድርጅት ስር ተሰባስበው እና አድማ በማድረግ ከጥቅምት 29 ቀን 1997 ዓ.ም. እስከ ህዳር 05 ቀን 1998 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ከአንድ ጎሳ የመጡ ናቸው በሚሏቸው ላይ ጥቃት በመሰንዘርና በማጥላላት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ድርጅት አባልና ደጋፊ የሆኑትን ሕዝቡ እንዲያገል አመራር በመስጠት፣ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍ

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *