በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በተከሰሱ ዜጎች ላይ 35 ሰዎችን የዐቃቤ- ሕግ ምስክር አድርጎ ማቅረብ ጀመረ

SHARE THIS TAGS የአቶ መለስ መንግሥት በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ (112546) በከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና ነፃ አሳቢ ዜጎች ላይ 35 ሰዎችን የዐቃቤ- ሕግ ምሥክር አድርጎ ማቅረብ ጀመረ። መንግሥት የምስክሮቹን የቀን ውሎ አበል፣ የቁርስ፣ ምሳ ፣ እራት የምግብ ፍጆታ በመሸፈን ሌሎች ጥቅማ- ጥቅሞችን እንደሚያስብ የፍርድ ቤት ምንጮች አስታወቁ፡፡ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ትላንት ለሙሉ ቀን በእነ አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በተከሰሱት የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት፣ ነፃ አሳቢ ዜጎችና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ የቀረቡት የዐቃቤ- ሕግ የሰው ምስክሮች በሦስት ደረጃ የተከፈሉ ሲሆን አንደኛ ማስረጃዎቹ የተገኙበትን ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱ ታዛቢዎች፣ ሁለተኛ በ”ሽብርተኝነት ወንጀል‘ የገንዘብ ዝውውር እና የሽብር ተግባር ጽሑፎች በመጻፍ፣ በማተም እና ለመበተን በመዘጋጀት ባለማወቅና በቀናነት ተሳታፊ የነበሩ መስካሪዎች እና በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው ተብሎ በዐቃቤ- ሕግ የምስክርነት ጭብጥ ላይ ተብራርቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትላንት ለሙሉ ቀን በዋለው ችሎት 21 የዐቃቤ- ሕግ ምሥክሮችን በጋዜጠኛና ፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ፣ በአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌ፣ በአንድነት ፓርቲ አመራር አባል ናትናኤል መኮንን፣ በአንዷለም አያሌው እና በክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ላይ ያደመጠ ሲሆን ቀሪዎቹን እና በዋናነት የወንጀል ድርጊቱ ተሳትፎና እውቀት ነበራቸው የተባሉትን (ከእስር የተፈቱ ምስክሮች) ለማድመጥ ለሰኞ ታህሳስ 9 ቀን 2004 ዓም ለማድመጥ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ዓርብ ታህሳስ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ለሙሉ ቀን ከቀረቡት 21 ምሥክሮች ውስጥ ሪፖርተራችን ያናገራቸው ሁለት ወንድና አንዲት ሴት የአንደኛ ደረጃ የታዛቢነት ምስክር እና የሁለተኛው ደረጃ በተዘዋዋሪ ባለማወቅ በድርጊቱ ተሳታፊ የተባሉት ምሥክሮች በተደጋጋሚ በዐቃቤ- ሕግ ምን እንደሚሉ እንደተነገራቸው ለሪፖርተራችን ገልጸው፣ ሰኞ ታህሳስ 2 ቀን ለመጨረሻ ጊዜ ለሙሉ ቀን በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ የፍርድ ቤት ገጽታ ተዘጋጅቶ በዐቃቤ-ሕጎችና በመርማሪ ፖሊሶች የምሥክርነት አሰጣጥ ልምምድ መውሰዳቸውንና የፍርድ ቤቱ ግን ከበድ እንደሚልና በመስቀለኛ ጥያቄዎች ብዛት ከአጠናነው ውጪ በራሳቸው መንገድ ለመናገር ተገደናል ብለዋል፡፡ ሃሙስ ታህሳስ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ማለዳ ላይ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተሰባስበው ወደ ውስጥ መስታወቱ በማያሳይ ሰርቪስ ልደታ ፍርድ ቤት አምጥተዋቸው ለምስክርነት ተሰናድተው እንደነበር የገለጹት እነዚህ የዐቃቤ- ሕግ ምሥክሮች ፣ በወቅቱ ፍርድ ቤቱ የምስክርነት ሂደቱን ለዓርብ በመወሰኑ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መልሰው በልምምድ ወቅት እንደሚደረግላቸው ሁሉ ምሳቸውን እንደጋበዟቸውና ወደ ኋላ የባከነውን ጊዜያቸውን ታሳቢ ያደረገ ውሎ አበል እንዳለ እንደተገለጠላቸው፣ ነገር ግን በሦስተኛ ደረጃ ከወንጀሉ ጋር ቀጥታ ተሳትፎ ነበራቸው የተባሉት የዐቃቤ- ሕግ ምስክሮች ከእኛ ጋር ሳይቀላቀሉ ቀርተዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሪፖርተራችን ያናገራቸው አንድ የፍትህ ሚንስቴር ሠራተኛ ” እነዚህ ለታዛቢነት የተመረጡት ምሥክሮች ሁሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና በገንዘብም ሆነ በቁስ (ሥራ፣ የቀበሌ ቤት፣ አነስተኛ አርከበ ሱቅ ወዘተ) ከመንግሥት ማግኘት የሚፈልጉና ከዚህ ቀደም ያገኙ መሆናቸውን መንግሥት አውቆ እንደውለታ እንደሚቆጥርላቸው በተለያየ መንገድ ገልፆ የመለመላቸው ናቸው” ብለዋል፡፡

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *