የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአረብ-ሳት ወረደ ሲል ኢሳት ዘገበ

 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአረብ-ሳት ወረደ ሲል ኢሳት ዘገበ

 ኢሳት በሰኞ ነሐሴ 7 ፕሮግራሙ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በጠና መታመም እንዲሁም ስለ ሕልፈታቸዉ መዘገቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በመገናኛ ብዙኀኝ ላይ የሚያደርገዉን አፈናና ቁጥጥር ከምን ግዜዉም በላይ አጠናክሮ ቀጥሏል ያለ ሲሆን ፤ በቅርቡ “የኤርትራን የሳተላይት ቴሌቪዥን ያወከ ሲሆን በዚህ ተግባሩ ምክንያትም የኢትዮጵያ ቲሌቪዥን ከአረብ-ሳት የሳተላይት ስርጭት ታግዷል በማለት ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ቴሌቪዥን ላይ የሚፈፅመዉን የማወክ ተግባር ተከትሎ አረብ-ሳት የኢትዮጵያን መንግስት እኩይ ተግባር የማስቆም ህጋዊና ተቋማዊ ሀላፊነት አለበት ሲሉ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ባለስልጣናት መናገራቸዉን የጠቆመዉ የኢሳት ዘገባ የኤርትራ ቴሌቪዥን በሚታወክበት ጊዜ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት እንደነበር አያይዞ ጠቅሷል፡፡

በተያያዘም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የሆኑት አቶ ይሳቅ ያሬድ “ይህ የሚያሳየዉ “የኢትዮጵያ መንግስት ለቴክኖሎጅ ያለዉን ባዕድነትና የራሱ ቴሌቪዥን ዋጋ-ቢስነት ነዉ” ሲሉ ለሚዲያ ተቋማት መናገራቸዉን የጠቀሰ ሲሆን ፤ በማከልም “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ከይዘቱ ባሻገር የድምፅና ምስል ችግር ያለበት አማተር ስታንዳርድ ላይ እንኳ መድረስ ያልቻለ” ማለታቸዉን አያይዞ ጠቁሟል፡፡

የኤርትራ ቴሌቪዥን ዳሬክተር የሆኑት አቶ አስመላሽ አብረሀ በበኩላቸዉ “የኢትዮጵያ መንግስት የአየር ላይ ዉንብድና እዉነትን ለመጋፈጥ አቅም እንደሌላቸዉ ያሳያል” ማለታቸዉን አያይዞ ጠቅሷል፡፡

የኢሳት ቴሌቪዥን ስርጭት መጀመርን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት የሳተላይት ስርጭት ማፈኛ ቴክኖሎጅ ወደ ሀገር ቤት ማስገባቱን እና የኢሳትን አንዳንድ ፕሮግራሞች ማስተላለፍ በመጀመሩ የኤርትራ ቴሌቪዥን ከዚህ በፊትም መታወኩን የጠቀሰዉ የኢሳት ዘገባ ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአረብ-ሳት ወርዶ እንደ ነበር የጠቆመ ሲሆን ፤ አያይዞም የኢትዮጵያ መንግስት “የኤርትራን ቴሌቪዝን አላዉክም” በማለት ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ በሰኔ ወር ወደ አረብ-ሳት መመለሱን አስታዉሷል፡፡

ኢሳት በዚህ ዘገባዉ እንደጠቆመዉ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ስምምነት ከመቀበሉ በፊት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚያሰራጨዉን የኤርትራ ተቃዋሚወች ፕሮግራም ለማቋረጥና በምላሹም በኤርትራ ቴሌቪዥን በኩል የሚሰራጨዉን የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚወች ፕሮግራም እዲያቋርጡ በተለይም የኢሳትን ፕሮግራሞች ማስተላለፋቸዉን እንዲያቆሙ የኤርትራ መንግስትን ጠይቆ የነበር ሲሆን ፤ የኤርትራ መንግስት ግን አናቋርጥም!! ከፈለጋችሁ የኛን ተቃዋሚዎች ፕሮግራም በቀን ለ24 ሰዓት እናዳሻችሁ አሰራጩት በማለት ጥያቄዉን ውድቅ ሊያደርገዉ ችሏል፡፡

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *