መሳቂያው ፓርላማ!

ያው እንደሚታወቀው የፓርላማ አባላቱ የምክር ቤት ስብሰባ ለማድረግ ሲሄዱ ወረፋ አይጠብቁ እንጂ የሆነ ኮሜዲ ፊልም ለመታደም ሲኒማ ቤት እንደሚገቡ አድርገው እንደሚያስቡት የታወቀ ነው። ይሄ ካልታወቀ ትልቅ የመረጃ ክፍተት አለ ማለት ነው!

በተለይ በአቶ መለስ አስተዳደር ጊዜ አባላቱ በሙሉ ለሳቅ ለጨዋታ ተሰነዳድተው ነበር ምክር ቤት የሚመጡት። (ዛሬ ማን ያጫውተን ዛሬ ማን ያጫውተን….! አረ ማን ያስቀን አረ ማን ያስቀን!) ብለን እናስነካው እንዴ!?

የምር ግን ኢትዮጵያ በየ ነገስታቱ አለቃ ገብረሃናን የመሰሉ አጫዋችች ቤተ መንግስት አካባቢ አይጠፉም ነበር። በመንጌ ጊዜም አቶ ቆምጬ አምባው የአለቃ ገብረሃናን ያህል የኢሰፓ አባላትን እና የዘመኑን ሰው በድርጊታቸው ያዝናኑት ነበር ሲባል ሰምተናል።

በአቶ መለስ ጊዜ ግን ገብረሃናውም፣ ቆምጬ አምባውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እርሳቸው ነበሩ! (እዚች ጋ አንድ ማስታወቂያ አለኝ… “አቶ መለስን እስቲ ተዋቸው”  ለምትሉኝ ወዳጆቼ በሙሉ እንደዚህ አትብሉኝ! አልተዋቸውም። ጋሽ ሃይሌ እንዳሉትም የሳቸው ነገር የምንተወው አይደለም እየተወሱ እየተዘከሩ ለዘላለም ይኖራሉ! በዚህ ላይ ድርድር የለም) ሳቄ ሳይመጣ ከቅንፍ ልውጣ!

እና አቶ መለስ ከጠቅላይነታቸው በተጨማሪ የምክር ቤቱ አጫዋችም ነበሩ!

ታድያ ለሃያ አንድ አመታት ጨዋታ የለመደ ምክር ቤት ዛሬ ማን ያጫውተው? ዛሬ ማን ያስቀው? አቶ ሃይለማሪያም እንደሆኑ ከአቶ መለስ እስካሁን በቅጡ የኮረጁት ቁጣቸውን ብቻ ነው።

ሰሞኑን የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ “ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ህዝቧን እግዚአብሔር በበረከቱ ይጎብኝ” ብለው ሲናገሩ ሙሉ የምክር ቤት አባላቱ ከት ብለው ሲስቁ የሚያሳይ ቪዲዮ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ አይተናል።

በርግጠኝነት የፓርላማ አባላቱን ምን አሳቃችሁ? ብለን ብንጠይቃቸው “…እና ፓርላማ የመጣነው ምን ልናደርግ ነው!?|” ብለው ባይመልሱ ውርድ ከራሴ!

እውነታቸውን ነው ገና ለገና ዛሬ እርሳቸው ሞቱ ተብሎ ፓርላማው ሳይሳቅበት ይዋል እንዴ!?

የሚገርመው ግን “መለስ አልሞቱም” የሚለው ንግግር ያላሳቃቸው ተበካዮቻችን (በቅንፍ የታይፕ ግድፈት አለ የምትሉ እያስተካከላችሁ እንድታነቡ መፈቀዱን እገልፃለሁ!) “እግዚአብሔር ይባርከን!” ሲባል ከት ብለው መሳቃቸው ነው። ይሄኔ ነው መሳቀቅ ያለችው ማን ነበረች!?  ለማንኛውም ፓርላማውን መሳቂያ አድርገውት የሄዱት እሳቸው ናቸው እና አዎ መላቀቅ የለም “ዘላለም እንደተዘከሩ” ይኖራሉ!

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *