ግብፆች-የዲፕሎማሲ ጥረት የማይሳካላቸው ከሆነ በጦር ኃይል የኢትዮጵያን ግድቦች የማፈራረስ ዕቅድ

ሰሞኑን ዊኪሊክስ ምሥጋና ይድረሰውና ግብፆች ምን እንዳሰቡ ምስጢራቸውን አሾልኮባቸዋል፡፡ የዲፕሎማሲ ጥረት የማይሳካላቸው ከሆነ በጦር ኃይል የኢትዮጵያን ግድቦች የማፈራረስ ዕቅድ መያዛቸውን ነግሮናል፡፡ ዊኪሊክስ ትክክል ይሁን አይሁን ኢትዮጵያ በግዴለሽነት ልታየው አይገባም እላለሁ፡፡ ጊዜ ለመግዛት ይሁን ለማዘናጋት ግብፆች ሕዝባዊ ዲፕሎማቶች (Public Diplomats) በላኩ ሰሞን በኢትዮጵያ ውስጥ የግብፆች አመለካከት ተቀይሯል የሚል ሐሳብ ደጋግሞ ይነገር ነበር፡፡ ይህን ደግሞ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛ ሲያስተጋቡት ነበር፡፡ ምን ማረጋገጫ አለን ብሎ ጥያቄ የሚያነሳም አይሰማም ነበር፡፡
የተለየ ሐሳብ የሚያቀርብና የሚጠይቅ በሚዲያው አይቀርብም፡፡ ሐሳብ ሀብት መሆኑ ቀርቶ ይፈራል፡፡ ግን ሐሳብ በመኖሩ ሰው እንደ ዝንጀሮዎቹ (ሳይንስ ዘመድ ነን ይላል) ከመኖር ወጥቶ አሁን ካለበት ደርሷል፡፡ ሐሳብን እንደ ሀብት የማንቆጥር በመሆናችን እንፈራዋለን፤ እናፍነዋለን፡፡ ለማጥፋትም እንጥራለን፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ሲጠፉ ደግሞ ድንቁርና ይነግስና ባለንበት መርገጥ ከዚያም ወደኋላ መንሸራተት ይሆናል፡፡ እስከመቼ ይሆን በዚህ መልክ የሚቀጠለው? ግብፆች ተስማምተዋል፣ እከሌ የሚባለው ባለሥልጣናቸው ቃል ገብቶልናል፣ እከሌ የሚባለው ደግሞ በጆሯችን ሹክ ብሎናል፣ ጳጳሱና ሼኩ ገዝተዋል በሚል ተስፋና ምኞት ብቻ መኖር አገሪቱን ለአደጋ ማጋለጥ ነው የሚሆነው፡፡ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊትም ይሆናል፡፡ ባለፈው በመዘናጋታችን በሻዕቢያ ተወረናል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ከተከፈለ በኋላ ፍርድ ቤቱ ዋሽቶን መሬቱ የእናንተ ተብለን እንደ ፍርድ ቤቱ እኛም መዋሸታችን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
ስምምነቶችና ውሎች አስተማማኝ እንደማይሆኑና እንደማያስጥሉ የአገራችንና የዓለማችን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ መፍረስ ህያው ምስክር የሆነችውን ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ ከኢጣሊያ ወረራ አላስጣላትም፡፡ ሒትለር ስምምነቶችን ቀዳዶ ጥሎ ወረራ አካሂዷል፡፡ የዓለምን ሕግ ጉልበተኞች እንደሚመስላቸው እየጠመዘዙ እስከዛሬ ይጠቀሙበታል፣ ስለሆነም አያስጥልም፡፡ ከአውሮፓ ተሰደው ቅኝ ግዛት የመሠረቱት በሄዱበት ክፍለ አኀጉር ሁሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር የገቡትን ቃልና ውል እየሰረዙ አገራቸውን ቀምተዋቸዋል፡፡ እነሱንም እንደ እንስሳት ፓርክ ከተወሰነ ቦታ ላይ አጥረዋቸው ይገኛሉ፡፡
በሰው ደም፣ በንብረትና በፖለቲካ ድጋፍ ትልቅ ውለታ የተሠራለት ሻዕቢያ ለውለታውም ሆነ ለዝምድናው ቦታ ሳይሰጥ ወሮናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ስምምነትና ውል ትርጉም እንደሌለው መሪያቸው የተሸወደባቸውን ዘመዶቼ የሚዘፍኑትን ማዳመጥ ከምንም በላይ ስለውልና ስምምነት ያስረዳናል፡፡ ይኼውም ‹‹አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ፣ ሰው አማኙ›› ነው፡፡ ስለሆነም ለኢትዮጵያ ደኅንነት ብቸኛውና አስተማማኙ የቅድሚያ መከላከል የሚሊታሪ ዶክትሪን (Deterrance) ወይም ተያይዞ መጥፋትን ‹‹Mutual Assured Destruction (MAD)›› ፖሊሲ መከተልና ለዚህም ማስፈጸሚያ የሚሊታሪ አቅሟንም መገንባትና ዕቅድ ማውጣት አለባት፡፡ ይኸውም ግብፅ የኢትዮጵያን ግድብ በማንኛውም ዓይነት ማለትም በሰላም፣ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ በኃይል አደናቅፋለሁ፣ ጉዳት አደርሳለሁ ብላ ካሰበችና ከተንቀሳቀሰች የኢትዮጵያ የአፀፋ መልስ አስዋን ግድብን ማጥቃት መሆን አለበት፡፡
አስዋን ግድብን በማውደም ከግድቡ የሚያገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይል በማጥፋት ወደ ጨለማ ልንከታቸው እንደምንችል፣ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የሚያገኙትን የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሚያጡ፣ ከአስዋን ግድብ ጀምሮ ያሉት ከተሞቻቸው ከአሥር ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚኖርባትን ካይሮን ጭምር በጎርፍ ታጥበው ሜዴትሪንያን ባህር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ፣ የሰው ልጅ የሥልጣኔ አሻራና ቅርስ የሆኑት ፒራሚዶቻቸው በጎርፍ ሊጥለቀለቁና ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል የሚያስገነዝብ ፖሊሲና ስትራቴጂ ኢትዮጵያ መከተል አለባት፡፡ ይህንም ፖሊሲ ለግብፅና ለዓለም ሕዝብ በግልጽ ማሳወቅ የግድ ነው፡፡ ስለሆነም ግብፆች በኢትዮጵያ ላይ ከሚያደርሱት ውድመት በላይ እንደሚወድሙ ማሳወቅ፡፡ እነሱ ለሚያደርሱት ጥፋት የሚደርስባቸው ድርጊት የከፋና የበለጠ መሆኑን ብቻ ሲገነዘቡና ሲያውቁ በሰላም ተባብሮ መሥራትን ይመርጣሉ፡፡ ከኃይል አማራጭ ወጥተው በሰላም ለጋራ ጥቅም መሥራትን ይመርጣሉ፡፡
ግብፆች በውኃችን ሳንጠቀም ቀርተን በድንቁርና፣ በድህነትና በረሃብ እንድንሞት ከሆነ የሚሰጡን አማራጭ የተሻለው አማራጭ ሀብታችን የሆነውን ውኃችን እየተጠቀምን ከግብፅ ሊመጣ የሚችለውን ሞት መጋፈጥ ይሆናል፡፡ በግብፅም ሆነ በረሃብ መሞት ከሆነ የሚኖረን አማራጭ ከግብፅ የሚመጣውን ሞት መምረጥ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም በረሃብ፣ በድንቁርና በድህነት ሊያልቅ ከሚችለው ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር ከግብፅ ሊመጣ የሚችለው ሞት በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ፍትሐዊ ሞት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የአስዋንን ግድብ ለማጥቃት የሚያስችላት አቅምና ቴክኖሎጂ ገንብታ ዕቅድና ፕላን ይዛ መንቀሳቀስ አለባት፡፡ ለዚህም ሊረዷት የሚችሉ መንግሥታትን፣ በአገርም ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያን በሻማ ብርሃን ፈልጋና አስተባብራ አቅም ልትገነባ ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም አግኝታ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት ሊሳካ የሚችለው እኔ ሰላም ፈላጊና ሰላማዊ ነኝ እያለችና እየሰበከች እጆቿን አጣጥፋ ስለተቀመጠች ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን ከነካን የከፋ ኪሳራ ይደርስብናል ብለው እንዲያስቡ ማድረግ ስትችል ነው፡፡ ለዚህም አቅም ገንብቶ በተጠንቀቅ መቆም ያስፈልጋል፡፡ ሱዳንም ከግብፅ ጋር ትብብር አድርጋ ኢትዮጵያን አስጠቅታ ሱዳን የግድቦች፣ የድልድዮችና የወደብ ባለቤት ልትሆን እንደማትችል ኢትዮጵያ ልታስገነዝባት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ደርሶ በሰላም መኖር እንደማትችል ማሳወቁ ጊዜአቸውንና ሀብታቸውን ይቆጥብላቸዋል፡፡ ስለሆነም ግብፅና ሱዳን ከኃይል አማራጭ ወጥተው በሰላማዊና በጋራ መተባበር የማይለወጥ አቋም እንዲይዙ፣ የኃይል አማራጩ የማይሠራና የበለጠ ኪሳራ እንደሚያደርስባቸው ማስገንዘብና ለዚህም ማስፈጸሚያ ወታደራዊ አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ የኢትዮጵያ ደኅንነት ማስጠበቂያ ዋስትና ይሆናል፡፡ ውልና ስምምነት ላለመሰረዛቸውና ላለመተዋቸው ምንም ማስተማመኛ ተዓምር የለም፡፡
የኃይል ዕርምጃው ለግብፅም ሆነ ለሱዳን የሚያስከትለው ውጤት ኪሳራ ከሆነና ከአማራጭ ውጭ ከተደረገ፣ በጋራ ለዕድገት እንድንጠቀም በሰላም አብሮ መሥራትና የውኃውን ፍሰት የሚጨምሩ በሁሉም የተፋሰስ አገሮች የተደገፉ ፕሮጀክቶች መቅረፅ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በድርቅ እየተራቆቱ ያሉትን የኢትዮጵያ ተራሮች በደን መልሶ መሸፈን ማለት ነው፡፡ ከዚያም ተፈጥሮ የራሱን ሥራ እንዲሠራ ማድረግ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ወደ ሱዳንም ሆነ ወደ ግብፅ ሊሄድ የሚችለው ውኃ ከሚቀንሰው ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ የሚከሰተውን የደን ውድመትና በዚህ ምክንያት የሚደርሰው ድርቅ የበለጠ በውኃው መቀነስ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ግብፅም ሆነች ሱዳን ኢትዮጵያ በደን እንድትሸፈን በጀት መመደብና መርዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የሚያደርጉት እንጂ ለኢትዮጵያ ችሮታ አይደለም፡፡ በደን መራቆት ምክንያት ዓባይንና ተከዜን የሚገብሩት ገባር ወንዞች እየተዳከሙ ነው፡፡ ይዘውላቸው ሊሄዱ የሚችሉት ለም አፈርም እየተመናመነ ነው፡፡ ከአሁኑ ካልተሠራበት ለወደፊትም እየከፋ ነው የሚሄደው፡፡
ኢትዮጵያም አሁን ካለው የደን ተከላ የአንድ ሰሞን የዘመቻ አሠራር ወጥታ ቀጣይና ተከታታይ ያለው አሠራር መንደፍ አለባት እላለሁ፡፡ ለዚህ ዓይነት አሠራር ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፍራክሊን ዲ ሩዝቬልት ያቋቋሙት አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት (Great Depression) ለማውጣትና ለመታደግ ከነደፉዋቸው ፕሮግራሞች አንዱ ሥራ በመፍጠርና አካባቢን መልሶ በማገገም ትልቅ ሚና የተጫወተው  (Civilian Conservation Corps) ነው፡፡ ፕሮግራሙ በደን ውድመት ተራቁታ የነበረችውን አሜሪካ ታድጓታል፡፡ እስከ 90 በመቶ ደን ወድሞባቸው የነበሩ የአሜሪካ ግዛቶች ዛሬ አረንጓዴ የሆኑት በዚህ ፕሮግራም አማካይነት ነው፡፡ ፕሮግራሙ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሥራ ፈጥሮ ነበር፡፡
ለእኛም አገር እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም ቢቀረፅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን በተለይም ለጎዳና ተዳዳሪዎች ዜጎቻችን ሥራ ሊፈጥር ይችላል፡፡ አገራችንም ልምላሜዋን እንደገና እንድታገኝ፣ የዱር አራዊቶችም መጠለያ እንዲኖራቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በቂ ዝናብ እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ ለአየር መዛባት መቀነስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ ውጭ ደግሞ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በተለይ ግብፅና ሱዳን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ደኑን እንዲሸፍኑ ማስረዳትና ማግባባት ያስፈልጋል፡፡ የዓለም አየር ሙቀት መጨመር የሚያሳስባቸውም ፕሮግራሙን በገንዘብ እንዲደግፉት ማድረግ ይቻላል፡፡
ይህን ፕሮግራም ግብፆች እንዲደግፉት ግን ሌላኛው አማራጫቸው ማለትም በኃይል የኢትዮጵያን ግድብ ለማፍረስ መሞከር የበለጠ ኪሳራ እንደሚያመጣ፣ የአስቀድሞ መከላከል ወይም ለሚያደርሱት ጥፋት የበለጠ ጥቃት እንደሚገጥማቸው ሲገነዘቡ ነው እላለሁ፡፡

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *