ሪፖርተር – ‹‹ከአሁን በኋላ ትልቁ ሥራችን ወደ ሕዝቡ መሄድ ነው›› ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር

 On Sunday, January 1, 2012 11:02 PM.

የመድረክ አባል የሆነው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ ሁኔታ ጐላ ያለ እንቅስቃሴ እያካሄደ መጥቷል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ረጅም ጊዜ የወሰደ የውስጥ ግምገማ ካካሄደ በኋላ ፓርቲው የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ሰነድ ለማዘጋጀት መቻሉ ይነገራል፡፡ አንድነት ፓርቲ ፍኖተ ነፃነት የተሰኘ ልሳኑን በየሳምንቱ ያሳትማል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ምሁራንን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትንተና የሚሰጡበትን የውይይት መድረክ ያዘጋጃል፡፡ አንድነት ከምርጫ 2002 በኋላ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ላይ ኃይሌ ሙሉ የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫ 2002 በኋላ ፓርቲው በፖለቲካው ረገድ እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ፓርቲው በሁለት መንገድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ እንሠራለን፡፡ በአገር ቤት በአዲስ አበባና በየክልሎች የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ አንደኛው የምንንቀሳቀስበት ጉዳይ ፍኖተ ነፃነት የተሰኘውን የድርጅቱን ልሳን ማሳተም ነው፡፡ ጋዜጣውን በአዟሪዎችና በመዋቅሮቻችን በኩል ወደየክልሎች እንልካለን፡፡ አባሎችና ደጋፊዎቻችን ጥሩ እየሠራችሁ ነው ቀጥሉ በማለት ይደውሉልናል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ የፓርቲው መግለጫዎችና በጋዜጣችን የታተሙ ጽሑፎች በድረ ገጾች ይወጣሉ፡፡ የድርጅቱንና የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በየሳምንቱ ማውጣታችን በጥሩነቱ የሚገለጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል በጽሕፈት ቤታችን አዳራሽ ውይይቶች እናደርጋለን፡፡ በሒደት ሰው በብዛት መምጣት ጀምሯል፡፡ አንገብጋቢ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ በአገር ቤትና በውጭ አገር የሚኖሩ ምሁራን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡ ይህንን ስንመለከት በሕዝብ ግንኙነት በኩል ጥሩ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አሁን የሚቀረው ሌላው ሥራ ድርጅቱን በአዲስ መልክ ማደራጀት ነው፡፡ ከምርጫ 2002 በኋላ ባደረግነው ግምገማ የውስጥ አደረጃጀታችንን ማስተካከል አለብን ባልነው መሠረት እየሄድን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ ከተማ 23 ወረዳዎች ምክር ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡ ፓርቲው በየወረዳው እየተደራጀ ነው፡፡ የየወረዳው ምክር ቤቶች የራሳቸው ጽሕፈት ቤት አላቸው፡፡ የራሳቸው አካውንት አላቸው፡፡ የራሳቸው መዋቅር አላቸው፡፡ አሁን የሚቀረው ወደ ታች ማስፋት ነው፡፡ በክልሎችም ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ፓርቲ አሁን የመሠረተው አዲስ አደረጃጀት ከድሮው በምን ይለያል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከዚህ በፊት ከአገር ውስጥም ከውጭም የምናገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ወደ ክልል፣ ዞንና ወረዳ እንልክ ነበር፡፡ አሁን ይህንን እያስቀረን ነው፡፡ ወረዳዎች ራሳቸውን ችለው እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡ በወረዳ ደረጃ የሚሰበሰብ ገንዘብ ካለ 75 በመቶ እዚያው ለወረዳው ሥራ እንዲውል 25 በመቶው ወደ ዞን እንደተላለፉ ይደረጋል፡፡ ዞኑ ደግሞ 20 በመቶውን ወስዶ አምስት በመቶ ለማዕከል ይልካል፡፡ በዚህ መልኩ ራሳቸውን እየቻሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ትልቁን ምልክት ያየነው ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄድነው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ በጉባዔው የተሳተፉት በየክልሉ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች የራሳቸውን ወጪ ሸፍነው ነው የመጡት፡፡ ሪፖርተር፡- በየወረዳው የሚገኙ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በቂ የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣሉ ማለት ነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሰው ይፈራል፡፡ በዚያው ልክ የሚረዱ ደፋሮችም አሉ፡፡ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች በርከት አድርገው ይሰጣሉ፡፡ ከአደረጃጀት አኳያ ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኙ አባላትም እየጨመሩ መጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አቶ በረከት ስምኦን ሰሞኑን ባሳተሙት መጽሐፍ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው አርሶ አደሩ እንዲመርጣቸው እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ትችት እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ሁልጊዜ የፓርቲ እንቅስቃሴ የምናደርገው በየክልሉ በተደራጀው የፓርቲው መዋቅር አማካይነት ነው፡፡ ከማዕከል ተነስተን ሁሉንም 500 ወረዳዎች ለመድረስ አንችልም፡፡ እዚህ ማዕከል ሆነን እነሱን እናስተባብራለን፡፡ በእርግጥ ከምርጫ 2002 ወዲህ ትንሽ ደክመናል፡፡ ከምርጫው በፊት በብዙ ቦታዎች በርካታ ሕዝባዊ ስብሰባዎች አካሂደን ነበር፡፡ ከምርጫ በኋላ ግን በክልሎች ይቅርና በአዲስ አበባም ብዙ አልሠራንም፡፡ ግምገማ በማካሄድ ተጠምደን ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ብዙውን ጊዜ ዕቅድ የላቸውም ብሎ ሲናገር በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡ ኢሕአዴግ እንደዚያ ስላለ ሳይሆን እኛ በራሳችን ሁልጊዜ በኢሕአዴግ ላይ ጣታችንን መቀሰራችን ትክክል አይደለም፤ ራሳችንን ማየት አለብን ብለን 2003ን ራሳችን በመገምገም ነው ያጠናቀቅነው፡፡ ከግምገማው ተነስተን የስትራቴጂና የአምስት ዓመት ዕቅድ አውጥተናል፡፡ በእነኝህ ሥራዎች ላይ በመጠመዳችን ብዙ ወደ ሕዝብ አልሄድንም፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን አላካሄድንም፡፡ አሁን አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ተዋቅሮ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ ከአሁን በኋላ ትልቁ ሥራችን ወደ ሕዝቡ መሄድ ነው፡፡ የገመገምነው ዋና ጉዳይ በምርጫ ጊዜ ብቻ መንቀሳቀስ የለብንም የሚል ነው፡፡ በአንድ በኩል ድርጅታችን የማጠናከር ሥራ እየሠራን በሌላ በኩል ከሕዝብ ጋር እየተገናኘን መወያየት አለብን፡፡ ከአሁን ጀምሮ በዕጩ አመላመል ላይ በመነጋገርና ማኒፌስቶ በማዘጋጀት ወደ ምርጫው እናመራለን፡፡ በማዕከል በኩል ፓርቲው በየወረዳው የሚጠናከርበትን ሥራ እንሠራለን፡፡ ኢሕአዴግም እኮ የፓርቲ ሥራ የሚሠራው በመዋቅሮቹ በኩል እንጂ እነ አቶ መለስና እነ አቶ በረከት ወደ ሁሉም ቦታ እየሄዱ አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- ፓርቲው ያለው የገንዘብ አቅም ምን ይመስላል? አሁንም ከውጭ የገንዘብ ድጋፍ ታገኛላችሁ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ከምርጫ 97 ምርጫ በኋላ የታሠሩ የቅንጅት አመራሮች ከእስር ሲፈቱ ወደ አውሮፓና ወደ አሜሪካ ተሰማርተው ደጋፊዎችን አነጋግረው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በአመራሮቹ መፈታት የተደሰቱ ኢትዮጵያውያን ያደረጓቸው መዋጮዎች ነበሩ፡፡ መዋጮዎችን የሚያሰባስቡ ድጋፍ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ እስከ አሥራ ሰባት የድጋፍ ኮሚቴዎች አሉ፡፡ በአሜሪካ ሕግ መሠረት በሕጋዊነት ተቋቁመው ሥራ ይሠራሉ፡፡ የአንድነት ድጋፍ ማኅበራት ተብለው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በየጊዜው ከሚያገኟቸው ገንዘቦች ይረዱናል፡፡ በተለይ በምርጫ 2002 ብዙ ደግፈውናል፡፡ በእርግጥ ከምርጫ 97 በኋላ ቅንጅት ሲከፋፈል የድጋፍ ማኅበራት የተከፋፈሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተለይ ደግሞ በሰላማዊ ትግል ተስፋ የቆረጡ አንዳንድ ግለሰቦች ወደ ግንቦት 7 አዘንብለዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ከውጭ የምናገኘው ድጋፍ ከነጭራሹ አልቆመም፡፡ ፓርቲያችን በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል ራሱን መቻል አለበት ብለን ትኩረት ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ያለነው ሁልጊዜ ከውጭ በሚመጣ ዕርዳታ ተወስነን መቀመጥ የለብንም በሚል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ መድረክን በተለይም አንድነት ፓርቲን ከሽብርተኝነት ጋር በተገናኘ ይወነጅላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር አንድነት ራሱን ሊያጠራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ ኢሕአዴግ እንደሚለው ፓርቲያችሁ ያልጠራ ነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- እኛ በአቋም ደረጃ ሰላማዊና ሕጋዊ የምርጫ ፓርቲ ነን፡፡ ይህንን የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው አባሎቻችን የሚሆኑት፡፡ ከዚህ ውጭ መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው በግልጽ ለአባሎቻችን ነግረናል፡፡ ችግር ያለባቸው ሰዎች ካሉ በግል መከታተል ከባድ ነው፡፡ እያንዳንዱን ግለሰብ መከታተልና መቆጣጠር የእኛ ሥራ አይደለም፡፡ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አሉባችሁ ብሎ ከሚያስፈራራ ወይም ስም ከሚያጠፋ እከሌ እከሌ ወንጀል አለበት ትጠየቃላችሁና አስተካክሉ ብሎ ለእኛ ሊነግር ይገባ ነበር፡፡ እውነት ቅንነት ካለው፡፡ ካለበለዚያ በሕገ መንግሥቱና በሕጉ መሠረት አስሯቸው ወንጀለኛ መሆናቸውን በፍርድ ቤት አረጋግጦ ሊቀጣ ይችላል፡፡ በእኛ በኩል ግን ወንጀል የፈጸሙ አባላት የሉንም፡፡ መንግሥት በሽብርተኝነት ይከሰናል እኛ ግን ምክንያት የለህም ነው የምንለው፡፡ የፓርቲያችን አመራር አባላት የሆኑት አንዱአለምና ናትናኤል ታስረዋል፡፡ እስካሁን ባየሁት የሰነድ ማስረጃ እነዚህን ሰዎች በሽብርተኝነት የሚያስከስስና ከግንቦት 7 ጋር የሚያያይዛቸው ነገር አላየሁም፡፡ እንግዲህ ውጤቱን እናያለን፡፡

አቶ አንዱአለም እንደ ሕዝብ ግንኙነት ሊቀመንበርነቱ የድርጅቱን አቋም ነው የሚያንጻባርቀው፡፡ እኛ እስከምናውቀው ድረስ በሰላማዊ ትግል የነማርቲን ሉተር ኪንግና የነጋንዲ ደቀመዝሙር ነው፡፡ መንግሥት እኛን በሽብርተኝነት የሚከስበት መሠረት የለውም፡፡ ሌሎቹ ለመብታቸው የሚታገሉት ኦሮሞዎች (በኦህኮም ይሁን በኦፌዴን) የኦነግ ተከታዮቹ ናቸው ተብለው ይወነጀላሉ፡፡ እኔም ኢሕአዴግ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ የሚደረገውን አውቃለሁ፡፡ ትንሽ ስለ ኦሮሞ መብት የምትከራከር ከሆነ ‹‹ይሄማ ጠባብ ነው፤ ይሄማ የኦነግ ተከታይ ነው፤›› ተብለህ የምትወነጀልበት ሁኔታ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ካልሆነ ታዲያ ኢሕአዴግ አንድነትን የሚወነጅለው ለምንድነው ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በአገር ውስጥም በውጭ አገርም ብዙ ድጋፍ እንዳለን ያውቃል፡፡ ከኢሕአዴግ የተለየ ፕሮግራም አዘጋጅተናል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ያንን ፕሮግራም ሕዝቡ ይቀበለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ተጠናክረው ከሄዱ ፈተና ይሆኑብኛል፤ ያቀድኩትን በሥልጣን ላይ የመቆየት ዓላማዬን ያጨናግፉብኛል ብሎ በማሰብ የሚፈጥረው ውንጀላ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንድ በኩል ጠንካራ አመራሮች እንዳይወጡ በሌላ በኩል ደግሞ ጠንክረን እሱን እንዳንቀናቀን ለማድረግ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አንድነት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን ግንባር ፈጥሯል፡፡ ይህ ግንባር ወደ ውህደት እንዲያመራ ከሚፈልጉት ፓርቲዎች መካከል ዋነኛ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ለምንድነው ውህደቱን የፈለጋችሁት? የተለያየ ርዕዮተ ዓለም እንደምትከተሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ልዩነት ውህደት ለመፍጠት አያስቸግርም?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ውህደቱ የሚጠቅመው መድረክ ውስጥ ያሉትን ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በርካታ ፓርቲዎች ነው፡፡ ዓላማቸውና ራዕያቸው አንድ ዓይነት ሆኖ እያለ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ተበታትነው ነው ያሉት፡፡ በአገሪቱ አሉ የሚባሉት ከዘጠና በላይ ፓርቲዎች ለምን ያስፈልጋሉ? ቢሰባሰቡ ተመራጭ ነው፡፡ ስትዋሀድ አባላት ይበዙልሃል፤ ጉልበትህና የገንዘብ አቅምህ ይጠናከራል፡፡ አመራሩ ወጥ በሚሆንበት ጊዜ ሥራዎች በብቃት ይሠራሉ፡፡ አንድነት ይህንን ጉዳይ እንደፍላጎት ይገልጻል እንጂ የመድረክ አባል ፓርቲዎች በግድ ይዋሃዱ የሚል ዓላማ የለውም፡፡ በርዕዮተ ዓለምም ሆነ ከዓላማ አንፃር የተለያዩ ፓርቲዎች ናቸው ተቀናጅተው አብረው በመሥራት ግንባር መመሥረት የቻሉት፡፡ አሁን 65 ገጽ ያለው ፕሮግራም አለን፡፡ ያንን ተግባራዊ በማድረግ በጋራ ተንቀሳቅሰን እየተዋወቅንና በጣም እየተቀራረብን በምንሄድበት ጊዜ ወደ መዋሀዱ እንመጣለን የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ይህንን ስናደርግ ኢሕአዴግን የሚቀናቀን ጠንካራ ፓርቲ መመሥረት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- በክልል፣ በዞንና በወረዳ ያሉ አባሎቻችሁ በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ አባሎቻችን የመንግሥት ሠራተኛ ከሆኑ ከመንግሥት ሥራ ይፈናቀላሉ፡፡ አርሶ አደሮችም ከመሬታቸው የሚፈናቀሉበት ሁኔታ አለ፡፡ የሚደበደቡም አሉ፡፡ ያለምክንያት በሐሰት ወንጀል ተከሰው የሚታሰሩ ብዙ ናቸው፡፡ አባሎቻችን ብዙ ችግሮችን ተቋቁመው ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት፡፡ ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የተሰበሰበው የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት እርስዎ ያቀረቧቸውን የሥራ አስፈጻሚ አባላት ተቀብሎ አፅድቋል፡፡ እነዚህ የሥራ አስፈጻሚ አባላት በምን መስፈርት ነው የተመረጡት? አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አንድነት ፓርቲ አሁንም በአዛውንቶች የተሞላ ነው ይላሉ፡፡

ዶ/ር ነጋሶ፡- የድርጅቱን ሕገ ደንብ አሻሽለናል፡፡ አንዱ ማሻሻያ የተደረገው በሊቀመንበሩ አመራረጥ ላይ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሊቀመንበሩን የሚመርጠው ሁለተኛ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ምክር ቤቱ ነበር፡፡ አሁን ግን ሊቀመንበሩ በጠቅላላ ጉባዔ እንዲመረጥ ተደርጓል፡፡ ሊቀመንበሩ ዕጩ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ይመርጣል፡፡ የድርጅቱን ስትራቴጂና የአምስት ዓመት ዕቅድ ማስፈጸም ይችላሉ ያላቸውን ሰዎች ይመለምላል፤ ለብሔራዊ ምክር ቤት አቅርቦ ያስፀድቃል፡፡ ይህ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ድርጅቱን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚያውቁ ሰዎች በአመራሩ ውስጥ ቢቆዩ ጥሩ ነው፡፡ አዳዲስ ኃይል ቢገባ ጥሩ ነው የሚል ሐሳብም አለ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ከብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጋር ተዋህደናል፡፡ የዱሮው የብርሃን አባላት ቅድመ ውህደት ከፈጸምን በኋላ በየኮሚቴው ገብተው ይሠሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ አባል ስለሆኑ ለእነሱም ቦታ መስጠት ያስፈልግ ነበር፡፡ የፕሮፌሽን ጉዳይም አለ፡፡ ተመራጩ በሚሠራበት መስክ በትምህርትም በተሞክሮም ብቃት አለው ወይ? የሚለውንም ታያለህ፡፡ የዕድሜና የጾታ ጉዳይ አለ፡፡ በድሮው ሕገ ደንብ መሠረት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ቁጥር 18 ነበር፡፡ የስትራቴጂ ሰነዱን ካዘጋጀን በኋላ ወደ 13 ቀንሰነዋል፡፡ አሁን በተሻሻለው ሕገ ደንብ ደግሞ ወደ 11 ዝቅ ብሏል፡፡ አሥር ሰዎችን መመልመል በጣም ከባድ ነው፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፣ አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ አስራት ጣሴ፣ አቶ ሽመልስ፣ አቶ ግርማ ሰይፉና እኔ የቀድሞው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ነን፡፡ ሌሎቹ አዲሶች ናቸው፡፡ ከዕድሜ አንፃር እስከ 45 ዓመት ዕድሜ የደረሱት የሥራ አስፈጻሚ አባላት 60 በመቶ ናቸው፡፡ አርባ በመቶ የምንሆነው ሥራ አስፈጻሚዎች ደግሞ ከ58 እስከ 74 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የምንገኝ ነን፡፡ ስለዚህ በዕድሜ ስብጥር በኩል የሚያሳማን ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በቀጣዩ ዓመት የአዲስ አበባ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ረገድ ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ነጋሶ፡- ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ሦስት ሰዎች ነን የተወዳደርነው፡፡ ከሦስታችን መካከል ዶ/ር ንጋት ጠንካራ ሰው ናቸው፡፡ ከእኔ ጋር ሲነፃፀሩም በዕድሜ ወጣት ናቸው፡፡ በብዙ ነገር ከእኔ ይሻላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምንም እንኳን ነጋሶ ከእኔ ይሻላል ብለው ራሳቸውን ከሊቀመንበርነት ፉክክር ቢያገሉም ከእኔ የተሻሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዶ/ር ንጋት ጠንካራ ሰው ስለሆኑ የአዲስ አበባን ምክር ቤት እንዲመሩ አድርገናቸዋል፡፡ የአዲስ አበባን መዋቅር በማደራጀት በሃያ ሦስቱም ወረዳ ያሉ አመራር አባላት በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ሌላው ከአሁን ጀምሮ ከታች ያሉትን መዋቅሮች ይዞ ከሕዝብ ጋር የመገናኘት ሥራ መሥራት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕዝቡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ሳያዝንብን አይቀርም፡፡ ብዙ መነጋገሪያ ጉዳዮች እያሉ እስካሁን ቀርበን አላነጋገርነውም፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ የመሬት ሊዝ ሕግ ትልቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይ እንኳን ሕዝቡን ጠርተን አላነጋገርንም፡፡ ሽብርተኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከአሁን ጀምሮ ከሕዝቡ ጋር መወያየት አለብን፡፡ ለእዚህም እየተዘጋጀን ነው፡፡ በአዲሱ የአዲስ አበባ ምርጫ አደረጃጀት ስንት ሰዎች ናቸው የሚቀርቡት? በወረዳና በክልል ደረጃ እንዴት ነው አወቃቀሩ? የሚለውን ጉዳይ በማጥናት ዕጩዎችን በማቅረብ ረገድ ለመዘጋጀት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ለምርጫ በዕጩነት የሚቀርቡት ሰዎች ብቃት ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ይህንን በተመለከተም ሥራ መሥራት ጀምረናል፡፡

በአጠቃላይ የመድረክ የምርጫ ማኒፌስቶ የሚዘጋጅ ቢሆንም ሁሉም ክልል የየራሱ የተለየ ባህሪ አለው፡፡ አዲስ አበባን በተመለከተ ምን ዓይነት አስተዳደራዊ፣ የፍትሕ፣ የፀጥታ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታዎች አሉ? ምን ችግሮች አሉ? ሕዝቡ ለውጥ የሚፈልግባቸው ጉዳዮች ምንድናቸው? የሚለውን በማጥናት ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ ወደ ምርጫ መግባት ስለሚያስፈልግ በዚህ ላይ መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመድረክም ጋር እንወያያለን፡፡ መድረክ የተመሠረተው ሰጥቶ በመቀበል መርህ ነው፡፡ በ2002 ምርጫ ችግሮች ነበሩ፡፡ በየትኛው ክልል ማን ይግባ በሚለው ጉዳይ ላይ ተስማምተናል፡፡ አንድ ድርጅት በአንድ አካባቢ እስከ 45 በመቶ ዕጩዎች ያቀርባል፡፡ ቀሪውን 55 በመቶ ሌሎች ፓርቲዎች ይከፋፈሉታል፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች ከሌሉ እዚያ አካባቢ ያለው ፓርቲ ተጨማሪዎቹን ዕጩዎች ያቀርባል፡፡ በዚህ ዓይነት የአዲስ አበባውን ሁኔታ አጣርተን በስምምነታችን መሠረት ከስድስቱ ፓርቲዎች ማን የት እንደሚወዳደር እንወስናለን፡፡ የመወያየቱንም ሥራ እንጀምራለን፡፡ ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ግን ፓርቲው በቀጣዩ የአዲስ አበባ ምርጫ መሳተፉን በሚመለከት በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል አመላክተዋል፡፡

ዶ/ር ነጋሱ፡- የምርጫ ፓርቲ ነንና ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ተዘጋጅተን መቅረብ አለብን፡፡ ምርጫ ይካሄዳል ወይስ አይካሄድም? እኛም ሆነ መድረክ በምርጫው ይሳተፋሉ ወይስ አይሳተፉም? የሚለውን የሚወስነው የፖለቲካው ምኅዳር ነው፡፡ እንደ 2002 ምርጫ ከሆነ አጠራጣሪ ነው፡፡ እያወቅን እንገባለን ወይስ አንገባም የሚለውን በሒደት እንወስናለን ብሎ መቀመጥ ሳይሆን፣ ከአሁኑ የምርጫ ምኅዳሩና የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲስተካከል በተለያዩ መንገዶች መሥራት አለብን የሚል እምነት አለ፡፡ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ከመጮህ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ በመድረክ በኩል ከምርጫ በፊትም ከምርጫ በኋላም ከኢሕአዴግ ጋር እንደራደር ብለን ያስቀመጥናቸው ነጥቦች አሉ፡፡ በእነዚያ ነጥቦች ላይ ኢሕአዴግ ከእኛም ሆነ ከሌሎች እውነተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደር አለበት፡፡ ሕዝብም ግፊት ማድረግ አለበት፡፡ ሕዝቡ የራሱን መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ አለበት፡፡ በምርጫ ጊዜ ድምፁን በነፃነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲሰጥ የሚያስችለው መብት እንዲከበርለት ለመብቱ መከራከር አለበት፡፡ ይህንን እንዲጠይቅም ሕዝቡን እንጠራለን፡፡ በሌላ በኩልም ኢሕአዴግን የሚረዱት የዲፕሎማሲው ማኅበረሰቦችም እንዲመክሩት ጥረት እናደርጋለን፡፡

ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ እውነተኛ ምርጫ መሆን አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ያለ ትግል ሥልጣን ለመያዝ ይፈልጋሉ በማለት ኢሕአዴግ በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡ እኛ የምንፈልገው ይህንን አይደለም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተስተካክሎ ሕዝቡ የፈለገውን የሚመርጥበት ሁኔታ እንዲመቻች ነው የምንፈልገው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተስተካክሎ ኢሕአዴግ በሀቀኛ ምርጫ ካሸነፈ እንቀበላለን፡፡ እኛም ካሸነፍን ኢሕአዴግ መቀበል አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ ለዚህም ሜዳው ከአሁኑ መስተካከል እንዲጀምር እንጠይቃለን፡፡

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *