መሬት፣ መሬት፣ አንድ (ከፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም)

 On Monday, January 9, 2012 11:20 AM.

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

በኢትዮጵያ ባህላዊ አስተሳሰብ መሬት ከዜግነትም አልፎ ከሰውነት ጋር የተያያዘ ነው፤ መሬት የሌለው ሰው ሰው አይባልም፤ ሰው ካልሆነ ዜጋ ሊሆን አይችልም፤ ዜጋ ካልሆነ መብትም ሆነ ግዴታ የለውም፤ ባህላዊ እምነትም ወደዚሁ መደምደሚያ ያደርሰናል፤ በባህላችን የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ የማይፈቀድላቸው ሰዎች ነበሩ፤ ሰውም፣ ዜጋም ለመሆን የማይፈቀድላቸው ነበሩ፤ እነዚህ ባለጆች፣ ጠይቦች እየተባሉ በሸክላ ሥራ፣ በሽመና፣ በአንጥረኛነትና በቀጥቃጭነት ይኖሩ ነበር፤ በኤርትራና በትግራይ እስላሞችም የመሬት ባለቤት ለመሆን አይፈቀድላቸውም ነበረ ይባላል፤ በልማዳችን መብትና ግዴታቸውን የተገፈፉ ነበሩ ማለት ነው፤ ይህ ዘዴ (ዘዴ ነው፤) መጥፎና መሰረታዊ መብትን የሚጥስ መሆኑ የማይካድ ሆኖ ብዙ ከእርሻ ያልወጡ ማህበረሰቦች የሥራ ክፍፍልን ለመፍጠር የዘየዱት ነው፤ የስራ ክፍፍል መፍጠሩ ጥሩ ነገር ቢሆንም ሰዎቹን ከዜግነት ደረጃ ከዚያም አልፎ ከሰውነት ደረጃ ማስወጣቱ ግፍ ነበር፤ ትልቁ ቁም-ነገር የመሬት ባለቤትነት መብት ከዜግነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነበር፤ ስለዚህም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ማንም የውጭ አገር ሰው የመሬት ባለቤት ሊሆን አይችልም ነበር፤ የዚህ አቅዋም ትክክለኛነት የተመሰረተው መሬቱን ከውጭ ወራሪ ለመጠበቅ የህይወት መስዋእትነት እስከመክፈል ድረስ ግዴታ ያለበት ዜጋ መሆኑ ነው፤ የመዝመት ግዴታ ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡

አፄ ምኒልክ በባለጆች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለማስወገድ ቢያውጁም የመሬቱን ጉዳይ የነኩት አይመስለኝም፤ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመንም ከከተማዎች መስፋፋት ጋር የከተማ ቦታ መግዛት ለማንም ኢትዮጵያዊ ክፍት በመሆኑ ባለጆችም ይገዙ ነበር፣ እንዲያውም በስራቸው እየከበሩ በመሄዳቸው ይከበሩ ጀመር፤ ዱሮ ልጆቻቸውን ለባለጆች የማይድሩ ‹‹ጨዋዎች›› ሁሉ ለሀብታም ባለጆች መስጠት ተለመደ፤ (ባለጌን ገንዘቡ አያኮራውም የሚባለው በተግባር እየተሻረ ቀረ፤) በገጠርም የባለጆቹ ሀብታምነት በነሱ ላይ የነበረውን ንቀት በመጠኑም ቢሆን ቢያጠፋውም የእርሻ መሬት ለማግኘት አልቻሉም ነበር፤ በገጠር የነበረው የእርሻና የመኖርያ መሬት ዓጽመ-ርስት ወይም ርስት ነበር፤ ይህ በውርስ ወይም በአገር አገልግሎት ብቻ የሚገኝ ነበር፤ በኋላ ዘመናዊነት እየገፋ ሲሄድ አንዳንድ የእርሻ መሬት ለግዢ ክፍት ሆነ፡፡

ደርግ መጣና ከስልጣን በተገኘ አለማወቁ ቅጥ የሌለው አዋጅ አወጣ፤ (በአጋጣሚ የመሬት አዋጁን ረቂቅ አይቼ ከባድ ስህተቶች የመሰሉኝን ለይቼ እንዲታረም ጽፌ ለኮሎኔል መንግስቱ ሰጥቼው ነበር፤) አንደኛ የመሬት አዋጁ በሰሜንና በደቡብ ያለውን የመሬት ይዞታ ችግር ተመሳሳይ በማድረጉና ተመሳሳይ መፍትሔ በመስጠቱ ልክ አይደለም፤ የሰሜኑ ችግር መሬት ከትውልድ ወደትውልድ ሲተላለፍ እየተሸነሸነና እያነሰ መሄዱ ስለሆነ መፍትሔው ያንን ማገድ ነበር፤ ሁለተኛ በደቡብ ደግሞ ችግሩ አንዳንድ ሰዎች አገር-ምድሩን ሁሉ ይዘውት ብዙዎች ሰዎችን መንቀላቸው ነበረና ይህንን የዘረፉ ውጤት በፍትሐዊ ድልድል ማስተካከል ነበር፤ ሦስተኛው የአዋጁ ችግር ደርግ ማኘክና መዋጥ የማይችለውን መጉረሱ ነበር፤ ይህም በዚያን ዘመን ተጀምሮ የነበረውን ከፍተኛ የትላልቅ የእርሻ እድገት ማገዱ ነበር፤ እነዚህ ትላልቅ እርሻዎች መሬታቸው ተወርሶ ኪራይና ግብር እየከፈሉ እንዲቀጥሉ ቢደረግ ተጀምሮ የነበረው በጣም የሚያስደንቅ የእርሻ እድገት ተቋርጦ አይቀርም ነበር፤ አራተኛውና አስቂኙ የአዋጁ የአለማወቅ ኒሻን ለእያንዳንዱ ዜጋ አስር ሄክታር መስጠቱ ነው!

ዛሬ ደግሞ ሌሎች አላዋቂዎች ወንበሩ ላይ ወጡና መሬትን እንደጉልት ድንች ለአላፊ አግዳሚው ይቸረችሩት ጀምረዋል፤ ከጥቂት ሳምንቶች በፊት ሁለት ያማሩ ባለስልጣኖች ስለመሬት ይናገሩ ነበር፤ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል አለ አንዱ፤ እውነት ነው፤ ቀጠለና መሬት አይጨምርም አይቀንስም፤ አለ፤ ይህ ደግሞ ግማሽ እውነት ነው፤ የምን መሬት ነው የማይጨምረው፣ የማይቀንሰው? እንዲህ ያለ ግማሽ ውሸት ብዙ የአመራር ስህተቶችን ያስከትላል፤ ቀጠለና መሬት የግል ቢሆን በመጀመሪያ ላይ እድል የሚያገኙት ሰዎች ይቀራመቱትና ለሚቀጥለው ትውልድ መሬት አይኖርም! ቁርጥራጭ እውነት ብቻ ነው፤ የተናገረውም ሕግና ሥርዓት ላለው ማህበረሰብ ይሁን ወይም በጫካ ውስጥ ለሚኖሩ አልታወቀም፡፡

ከመሰረቱ እንጀምር፤ የአድዋ ጦርነት፣ የማይጨው ጦርነት፣ የኦጋዴን ጦርነት፣ በኋላ ደግሞ የባድም ጦርነት ለመሬት ሲባል የተደረጉ ናቸው፤ እርግጥ አንዳንዴ በተለያዩ ምክንያቶች ሰፊ የአገርን ቁራሽ በወንበር ልዋጭ ወይም በስጦታ ማስረከብ ይቻል ይሆናል፤ ቅድም የጠቀስኋቸው ባለስልጣኖች ከተናገሩት ውስጥም መሬት የህዝብ ነው ያሉት ለእኔ ሙሉ እውነት ሆኖ ጦርነቶቹን ሁሉና በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የከፈሉትን የመጨረሻ መስዋዕትነት የሚያስረዳ ነው፤ ለውጭ አገር ሰው መሬት አይሸጥም ሲባል የነበረበትም ምክንያት አባቶቻችን የሞቱበትንና በህይወታቸው ዋስትና የተያዘውን መሬት ለሌላ አንሰጥም በማለት ነው፤ ይህ ካልሆነ ለባድመ ለምን ተዋጋን? እነዚያ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ሁሉ ለምን ሞቱ? ለምን በባድም ምክንያት ለሌላ ጦርነት እንዘጋጃለን?

መሬትን ከወራሪ በሕይወታቸው የሚጠብቁ ዜጎች ናቸው፤ ዜጎች በመሬቱ ላይ ምንም መብት ከሌላቸው ከወራሪ ለመከላከልስ ምን ግዴታ አለባቸው?

መሬት የህዝብ ነው ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በመሬቱ ላይ መብት ሊኖረው አይገባም ማለት ሊሆን አይችልም፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ መሬት ህይወቱን እስከመሰዋት ድረስ ለመገበር ግዴታ አለበት ከተባለ የግዴታው ዋጋ የሆነውን መብቱን መንፈግ እንዴት ይቻላል? የአገሩ ሰው መሬት ሳያገኝ ለውጭ አገር ሰው መሬት በምንም መልኩ የሚታደለው በማን ፈቃድና ለማን ጥቅም ነው? ዜጎችን ለአገራችሁ ለመሞት ተሰለፉ፣ ነገር ግን የመሬት ባለቤትነት መብት ገንዘብ ላለው ሁሉ ብቻ ነው ማለት የሚያዋጣ ነው ወይ?

ገንዘብ ያለው የፈለገውን ያህል መሬት እንዲገዛ ከተፈቀደ አቶ አላሙዲን ብቻውን፣ ካስፈለገም ከባልንጀራው ጋር አገሩን በሙሉ ቢገዛስ? ከዚያ በኋላ ንጉሠ ነገሥት ቢባልስ? ጉዞአችን ወደኋላ መሆኑ በጣም ግልጽ አይሆንም?

Short URL: http://www.zehabesha.com/?p=3728

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *