ኢትዮጵያ በዊኪሊክስ ፋይሎች (ሊያነቡት የሚገባ)

 On Tuesday, January 10, 2012 08:57 AM.

አቢይ አፈወር

(ክፍል 4)

…የሴቶችን የትምህርት ይዞታ በተመለከተ ጥናት የሚያደርጉት ተመራማሪ በጨለንቆ ያደረጉትን የአንድ ሳምንት ቆይታ ጨርሰው ጁላይ 8 ቀን ነበር ወደ አወዳይ የተመለሱት። ሌሊቱንም በከተማዋ ከሚገኙ ሁለት የበጎ ፈቃድ መምህራን ወዳጆቻቸው ጋር ለማሳለፍ ፈቀዱ። “በሚቀጥለው ቀን ከጠዋቱ 1 ሰዓት ላይ ግን ያልተጠበቀ ነገር ተፈጸመ። 3ቱም ሰዎች ያደሩበት መኖሪያ ቤት በታጠቁ ፖሊሶች ተከበበ። ተመራማሪውና ሁለቱ የበጎ ፈቃድ መምህራን ተገደው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰዱ። ከታጣቂዎቹ ጋር የነበረ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰውም ‘መንግስት ነኝ’ ሲል ራሱን አስተዋወቃቸው።

 

“ይህ በሆነ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሌሎች 6 በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች ያረፉ የበጎ ፈቃድ መምህራን ከያሉበት ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያዋ መጡ።

 

ፖሊሶቹ እንግልት አድርሰውባቸው ስለነበር በተለይም ሶስቱ ሴቶች በከፍተኛ ጭንቀት ተናውጠው ነበር። በተያዙበት ወቅት አንዷ መምህርት ርቃኗ ሳይታይ ልብሷን ለመቀየር ብትፈልግም እንኳን አንዱ ፖሊስ ዘወር አልልም በማለት አስደንግጧታል።

 

“ዘጠኙ ሰዎች ለ2 ሰዓታት ያህል በጣቢያዋ ከታገቱ በኋላ የመጀመሪያዎቹ የእስራቸው ምክንያቶች ተነግሯቸው። የማስተማር ፈቃድ የላችሁም ተባሉ፤ እንደገናም ሽብርተኞች ጥቃት ሊፈጽሙባቸው በማሰባቸው የታሰሩተረ ለደህንነታቸው ሲባል መሆኑ ተነገራቸው። ከዚያ በፖሊስ መኪና ተጭነውና ሌላ አራት የፌደራል ታጣቂዎችን የያዘ መኪና አጅቧቸው ወደ አዲስ አባባ ጉዞ ጀመሩ።

 

“በመንገዳቸውም ሌሎች ከአቅራቢያው ከተሞች የተለቀሙ ሰባት የበጎ ፈቃድ መምህራን ተቀላቀሏቸው። አስራ ስድስቱም እስረኞች ተርበው ነበር። ገና እኩለ ቀን ላይ ምግብ ፍለጋ ቢማጸኑም በኢትዮጵያ ሰዓት  እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት  ድረስ ግን የሚላስ የሚቀመስ ማግኘት አልቻሉም።

 

“አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላም ቢሆን ስለታሰሩበት ምክንያት በወጉ ሊያስረዳቸው የቻለ ሹም አልተገኘም። ይሁንና አሁንም አሁንም የሚቀያየሩ የማይገቡና የሚየስቁ የተለያዩ ክሶች በምክንያትነት ተነግሯቸዋል። አንዴ  ‘ችሎታችሁ ከመምህርነት በላይ በመሆኑ’ የሚል ውንጀላ ቀረበባቸው። ቆይቶ ደግሞ ‘ተማሪዎቻችሁን ከሚገባቸው በላይ እንዲያውቁ በማድረጋችሁ’ በሚል ተወነጀሉ።

 

“16ቱ ሰዎች ከማንም ጋር የመገናኘትም ሆነ ህጉ የሚፈቅድላቸውን አንድ የስልክ ጥሪ የማድረግ መብታቸው አልተከበረላቸውም።”

 

———          ———–           ———-

 

ይህ ከላይ የቀረበው ሪፖርት በአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ አማካኝነት ተቀናብሮ ወደ ስቴት ዲፓርትመንት ከተላከ መልእክት ላይ የተነቀሰ ነው። ታሳሪዎቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን አይደሉም። አስራ አምስቱ አሜሪካዊያን ሲሆኑ አንዱ ደግሞ እንግሊዛዊ ናቸው። አስራ አራቱ መምህራን በአሜሪካን ኮሌጆች ውስጥ ተማሪዎች ሲሆኑ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ለማስተማር በተዘረጋው ፕሮግራም ውስጥ በጎ ፈቃደኞች ሆነው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ገና ሳምንታት ብቻ ነበር የተቆጠሩት። አብረዋቸው የታሰሩት እንግሊዛዊ የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ናቸው።

 

ተመራማሪው ጆን ክሌማንም አሜሪካዊ ሲሆኑ ከተማሪዎቹ ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው በጁን ወር መጀመሪያ ነበር በግላቸው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እኚህ ሰው ጥናታቸውን የጀመሩት ከሁሉም የሚመለከታቸው የክልል ባለስልጣናት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ቢሆንም ከህገ ወጥ እስርና መንግስታዊ እንግልት ግን መትረፍ አልቻሉም።

 

ይህንን ሪፖርት ጁላይ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ያስተላለፉት የአሜሪካው አምባሳደር ሮናልድ ያማማቶ የዜጎቻቸውን እስርና እንግልት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ላይ፦

 

“ይህ ዜጎቻችንን ያላንዳች ህጋዊ መሰረት በማሰር የኢትዮጵያ መንግስት ያሳየው ማናለብኝነት በሀገሪቱ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ ምን እንደሚመስልእንደ ናሙና ማሳየት የሚችል ነው። አሁንም አሁንም የሚለዋውጡትና ጭራሽም ግራ የሚያጋቡት ውንጀላዎቹ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት ስፍራ እንደሌለውና የኢትዮጵያ መንግስት ማንም ይሁን ማን ያሰጉኛል ብሎ ያሰባቸውን ሁሉ ለማሰር በይፋ አንባገነንነቱን እያሳየ መምጣቱን ነው የሚመሰክሩት። በነዚህ የአሜሪካን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ዓይን ያወጣ ድፍረት የሚያረጋግጠውም መንግስት በመላው ሀገሪቱ ይህንን መሰልና ከዚህም በእጅጉ የከፋ ግፎችን እየፈጸመ ስለመሆኑ በየእለቱ የሚደርሱን ሪፖርቶች ምን ያህል የሚታመኑ መሆናቸውን ነው።” ይላሉ አምባሳደር ያማማቶ።

 

እነዚህ አስራ አምስት አሜሪካዊያንና አንድ እንግሊዛዊ ያለአንዳች አጥጋቢ ምክንያት ለእስር የተዳረጉት የኢትዮጵያ ፓርላማ የጸረ ሽብር ህጉን ካጸደቀ ከ24 ሰዓታት በኋላ ነበር። ህጉ ምን ያህል ተለጣጭና ለሚያምታቱ ትርጉሞች የተመቻቸ ስለመሆኑ ጠንከር ያሉ ትችቶች በሰብአዊ ተሟጋቾች እንደቀረበበት ያማማቶ በዚሁ ሪፖርታቸው ላይ ዳግም አስታውሰዋል። የመንግስትን እርምጃም አጠንክረው አውግዘዋል። ከዚያም አልፈው ይህን መሰል መንግስታዊ ህገወጥ እስሮችና አስቂኝ ውንጀላዎች ከዚያን በፊትም ሆነ በኋላ በመላ ሀገሪቱ በስፋት የተያዘ ጉዳይ ስለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፏቸው ሪፖርቶች ላይ ያብራራሉ። እኛም ዛሬ በተለይም ንጹሀን ወንድምና እህቶቻችን ይህን በመሰሉ መሰረተ ቢስና አስቂኝ ውንጀላዎች እየተጎሳቆሉ በመሆኑና የተጠቀሱባቸው አንቀጾችም በፍጹም ጭካኔ እንደመሞላታቸው ርእሰ ጉዳዩን የምጥን ፍተሻችን ትኩረት እናደርገው ዘንድ ወደድኩ።

 

ዊኪሊክስ ኢትዮጵያን በተመለከተ ይፋ ካደረጋቸው መልእክቶች መሀል ከአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ የተላለፉ ብቻ እንኳን ከ1ሺህ 800 በላይ ሲሆኑ መንግስታዊ አፈናን፣ ህገወጥ እስርንና አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በተመለከተ በርካታ ሪፖርቶች ቀርበዋል። ለዛሬው እይታችንም አራት በተለያዩ ወቅቶች የተላለፉ ሪፖርቶችን ለናሙማነት መርጫለሁ። ሶስቱ በ2009 አንዱ ደግሞ በ2007 ዓ.ም የተላለፉ ናቸው። በቅድሚያ በመግቢያችን ያነሳናቸው ምዕራባዊያን የመንግስት ታጋቾችን በተመለከተ ቀጣዩን ሂደት ባጭሩ እንመልከት።

 

“አስረህ አምጣው – ክሱ በኋላ ይፈለጋል”

 

“ተመራማሪው ጆን ክሌማን ታሳሪዎቹ ከኤምባሲያቸው ጋር ግንኙነት እንዲያደርጉ ደጋግሞ ቢጠየቅም ሰሚ አላገኘም። እንዲያውም ዮሀንስ የተባለው የፖሊስ አዛዥ ‘አሁን እየፈጸምን ያለነው ህገ ወጥ ድርጊት ነው። ኤምባሲያችሁ ይህን ካወቀ ደግሞ ጣልቃ ልግባ ስለሚል -ያ እናንተን ለከፋ ችግር ይዳርጋችኋል።’ ሲል በግልጽ አስጠነቀቀው።” ይላል የአምባሳደሩ ሪፖርት።

 

የኢህአዴግ ባለስልጣናት የጠሉትን ሁሉ ‘እሰሩ’ ከማለት ውጭ ለክሱ አይነት ብዙም የሚጨነቁ አይደሉም። በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ በጋዜጠኞችና በሙያ ማህበራት መሪዎች ላይ ሲያደርጉ እንደኖሩት ሁሉ እነዚህን ተማሪዎችንም “ጠፍሩልኝ እንጅ ክሱ በኋላ ይፈለጋል” የሚሉ  ይመስላሉ። ለአስረጅ ያህልም የሚከተለውን የኤምባሲውን ሪፖርት እንመልከት።

 

“ታሳሪዎቹ አዲስ አበባ እንደደረሱ ወደ ኢሚግሬሽን ዋና መ/ቤት ተወሰዱ። የኢሚግሬሽኑ ኃላፊ መኮንን ግን ለምን ወደሱ እንደተላኩ የሚያውቅ አይመስልም። ስለዚህም እያንዳናዳቸውን በተናጥል እየጠራ ማነጋገር ጀመረ። በዚህም በምን መልኩ ሊወነጅናቸው እንደሚችል ሰበብ ማፈላለግ ያዘ። ከቃለ ምልልሱ እየተነሳም የተምታቱና መሰረተ ቢስ ክሶችን ይለጥፍባቸው ጀመር። “ችሎታችሁ ከቋንቋ አስተማሪነት በላይ ነው” በሚል ወነጀላቸው። “ልጆቹን ከሚመጥናቸው በላይ እውቀት ሰጥታችኋችኋል” ሲል ከሰሳቸው።

 

“ተማሪዎቹ ገና አዲስ አበባ አየር ማረፊያ እንደደረሱ ለሚያከናውኑት ተግባር የያዙት ቪዛ በቂ መሆኑ የተረጋገጡላቸው ቢሆንም “ትክክለኛውን አይነት ቪዛ ያለመያዝ” በሚልም ከመወንጀል ግን አልተረፉም። “ባልተመዘገበ ኤን.ጅ.ኦ. ስር ነው ያስተማራችሁትም” ተብለዋል።” ይላሉ አምባሳደር ያማማቶ።

 

እስረኞቹ  ሌሊቱን በጥበቃ ስር ካደሩ በኋላ በማግስቱ ከኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ላይ ለ6 ሰዓታት እንዲቀመጡ ተደርገዋል። ለሌላ ሁለት ተጨማሪ ሰአታት ደግሞ በመ/ቤት የእንግዶች መቀበያ አዳራሽ ውስጥ አገቷቸው።

 

የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዳንድ አስፈላጊ ቅጾችን ሞልታችሁ ወደ ስራችሁ ትመለሳላችሁ ብለዋቸው ስለነበር በጥበቃ ስር እንዳሉ በተስፋ ነበር የቆዩት። ይሁንና የኢህአዴግ ሹማምንት በዚያች አፍታ ከአገሪቷ ተደብቀው የሚወጡባቸውን በረራዎች እያመቻቹላቸው ነበር።

 

የሚያስገርመው ነገር ይህ ሁሉ ሲሆን ወዳጅ ሀገር የሆነችው የአሜሪካን ኤምባሲ ስለዜጎቿ መታሰርም ሆነ ከአገር የመባረር ዝግጅት የተነገረው ነገር አልነበረም። ስለ ሁኔታው አምባሳደሩ እንዲህ ይላሉ፦

 

“… በኋላ እንደተረዳነው ከሆነ ያመቻቹላቸው በረራዎች ወደ ዱባይ፣ ፍራንክፈርት፣ አምስተርዳምና የመን የሚበሩ ነበሩ። ይሁንና ተማሪዎቹ ወደ እነዚህ ሀገራት ካመሩ በኋላ ወደ አሜሪካ የሚወስዳቸው ሌሎች በረራዎች ማግኘት ይቻሉ አይቻሉ እንኳን ለማጣራት የሞከረ አልነበረም።

 

“እኛ ስለተማሪዎቹም ሆነ ስለተመራማሪው መታሰር ያወቅነው በኢትዮጵያ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆነው ሰው ሐሙስ ጠዋት መጥቶ ስለሁኔታው ካስረዳን በኋላ ነው።” ይላሉ።

 

ዜናው እንደደረሳቸውም በኤምባሲው ኮንሱላር ኦፊሰር በኩል ሩጫው ተጀመረ። ለሚመለከታቸውም የመንግስት ባለስልጣናት ሁሉ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸው ጀመር። የእስረኞቹን ማንነት እንዲያረጋግጡላቸው፤ የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበርና ክስ ተመስርቶባቸው ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ወተወቱ። ያም ሆኖ ግን አንድም መልስ መስጠት የሚችል ሹም ጠፋ። ኢሚግሬሽን አላውቅም አለ። የፌደራል ፖሊስም አልሰማሁም ብሎ ካደ። የውጭ ጉዳይ መ/ቤትም የማውቀው ነገር የለም ባይ ሆነ።

 

የኋላ ኋላ አምባሳደሩ ራሳቸው የውጭ ጉዳይ ሚ.ሩን፣ የደህንነት ጉዳይ ዳይሬክተሩንና ምክትላቸውን በቀጥታ ካነጋገሯቸው በኋላ ነበር ‘አዎ አስረናቸዋል’ የሚለውን ማረጋገጫ ያገኙት። ይሁንና የኮንስላር ኦፊሰሮች እስረኞቹን ማግኘት አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ ተማሪዎቹ በታሰሩበት የኢሚግሬሽን መ/ቤት ቢመላለሱም እንኳን ሊያነጋግራቸው እንኳ የፈቀደ ሹም አልነበረም።

 

ቅዳሜ ከሰአት በኋላ ከመ/ቤቱ ውጭ አምስት ሆነው ተገትረዋል። የሚያናግራቸው አጥተው ከ3 ሰዓታት በላይ ሲጠባበቁ ቆይተዋል። ድንገት ከህንጻው አንድ መስኮት በኩል አስግጎ የወጣ ጭንቅላት አዩ። አንዷ እስረኛ ተማሪ ነበረች። እጆቿን እያውለበለበችም ምልክት ሰጠቻቸው። …ሊያነጋግሯት ግን አልተሳካላቸውም።

 

ሁኔታው እየከፋ በመምጣቱ አምባሳደሩ በቀጥታ ከጠ/ሚ/ሩ ጋር ለመነጋገር ተገደዱ። በዚህም ቅዳሜ ማምሻው ላይም ተማሪዎቹን ማግኘት ቻሉ። ይህ ሲሆን ግን እስረኞቹ ከሀገር ሊባረሩ የሚወስዳቸውን በረራ በአየር ማረፊያ ሆነው እየተጠባበቁ ነበር። በወከባም የኤምባሲው ኦፊሰሮች ከአየር መንገድ ባልደረቦች ጋር በመሆን ተባራሪዎቹን በቀጥታ ወደ አሜሪካ ሊወስዳቸው የሚችል በረራ የማፈላለግና የማዛወር ጥረት ጀመሩ።

 

የአሜሪካ ኤምባሲ ኦፊሰሮች ኤየር ፖርት (አየር ማረፊያ) በተገኙበት ወቅት ግን መንግስት ካገታቸው ዜጎቻቸው መሀል አንድ ሰው የደረሰበት አልታወቀም ነበር። ይህ ሰው ተመራማሪው ጆን ክሌማን ነበር። ኤምባሲው ስለጆን ክሌማን አንድም አይነት መረጃ ሳይሰጠው ለመቆት ተገዷል። ይሁንና በኋላ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት በዚሁ ሪፖርት ላይ እንደሚከተለው አካቶታል።

 

“ተማሪዎቹ በእስር ከቆዩበት የኢሚግሬሽን መ/ቤት ወደ ኤርፖርት ከመጓዛቸው ከጥቂት አፍታ በፊት የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ተመራማሪውን ጆን ክሌማንን ነጥለው በመውሰድ እሱ ቀርቶ ምርምሩን መቀጠል እንደሚችል ነገሩት።

 

“ይሁንና እስረኞቹ እንደተወሰዱ ግን ክሌማን በአንድ ምልክት ያልተደረገባት መኪና ተጭኖ ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ተወሰደ። የጥናት ስራዎቹን ጨምሮ በእጁ ላይ የተገኙ ነገሮች ሁሉ ተወሰዱበት። ሁለት ሌሊቶችን ሌሎች ሰባት እስረኞች ባሉበት የእስር ክፍል ውስጥ ነው ታጉሮ ያሳለፈው።

 

“እንደተለመደው ከኤምባሲዬ ጋር አገናኙኝ የሚለው ውትወታው ሰሚ አላገኘም።

 

“ያነጋገረው የፖሊስ አዛዥም የታሰረበትን ምክንያት በተመለከተ ሌላ አዲስ አይነት ውንጀላ አቀረበለት። “በሀገሪቷ አብዮት ለማስነሳት ስትቀሰቅስና ያለህጋዊ ፈቃድ ስትንቀሳቀስ ነበር።” አለው።

 

“ሰኞ ጠዋት ክሌማን ወደ ፍርድ ቤት ተወሰደ። ጠበቃ የማግኘት መብቱ ያልተከበረለት ሲሆን የፍርድ ሂደቱም ያለ አስተርጓሚ ነበር። ፖሊስ መረጃ ለማሰባሰብ እንዲችል ዳኛው አራት ተጨማሪ የእስር ቀናት እንደፈቅዱለት ክሌማን የተረዳው አንድ በወቅቱ በዚያ ችሎት የተገኘ ሌላ ታሳሪ ተርጉሞ ሲነግረው ነበር።” ይላል የሮናልድ ያማማቶ ሪፖርት።

 

የአሜሪካ ኢምባሲ ጆን ክሌማን የደረሰበትን ሳያውቅ ነው የቆየው። የህግ የበላይነት ትርጉም ባጣባት ኢትዮጵያ የትኛውም አይነት የተጻፈ ህግ ዋጋ እንደሌለውና ወሳኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ እንደሆኑ የአሜሪካ ኤምባሲው የተረዳው ይመስላል።

 

በዚህም ጆን ክሌማን ተገቢው የኮንሱላር ድጋፍ እንዲያገኝ የተፈቀደለትና የዋስ መብቱ የተጠበቀለት የአምባሳደር ያማማቶ ዳግም ጠ/ሚኒስትሩን በቀጥታ ካነጋገሩ በኃላ ነበር።

“ ጠ/ሚ/ሩ እስከፈቀዱበት ጊዜ ድረስ ሌላው ቀርቶ ክሌማን እስር ላይ ስለመሆኑ እንኳን ማረጋገጥ አልቻልንምነበር።” ነው ያሉት አምባሳደር ያማማቶ። አምባሳደሩ በዚህ ወደ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤታቸው በላኩት ሪፖርት መደምደሚያ ላይ ጠንካራ አስተያየታቸውን አካተዋል።

 

“ለዚህ በዜጎቻችን ላይ ለደረሰው ህገወጥ እርምጃ ተጠያቂ የምናደርገው የኢትዮጵያ መንግስትን ነው። ምንም እንኳን ሀገሪቱ የቪየና ኮንቬንሽንን ባትፈርምም ስምምነቱን ግን ልታከብር ይገባታል። ዜጎቻችንን አስራ ኢምባሲያችንን ያለማሳወቋ መሪዎቿ ምን ያህል ህጉን ጥሰው ለመራመድ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው።” የሚሉት ያማማቶ እርምጃውን በጽኑ ከማውገዝ ጋር ይህን መሰሉ ህገወጥ መንግስታዊ ጥቃት በኢትዮጵአዊያን ላይማ በየእለቱ የሚፈጸሙ ስለመሆኑ ያሏቸውን መረጃዎች አስታውሰዋል። በአጸፋው መንግስታቸው መውሰድ ስላለበት ርምጃም አስተያየታቸውን አክለዋል።

 

ይህ በምእራባዊያን ዜጎች ላይ የታየው መንግስታዊ ማንአለብኝነት አስገራሚ ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ በየእለቱ የሚወሰዱት ዘግናኝ ግፎች አንጻር ሲታይ ግን ያን ያህል ሊያስደንቅ አይገባም።

 

የአሜሪካን ኤምባሲ በየእለቱ ከሚደርሱት ሪፖርቶች መሀል እያበጠረ ያጠናቀራቸውና በተለይም ኦፊሰሮቹ በትእግስት የከወኗቸው የምርመራ ውጤቶች ያጋለጧቸው በርካታ ዘግናኝ የቅርብ ታሪኮች አሉ።

 

በዊኪሊክስ አማካኝነት ይፋ ከወጡ የተለያዩ ሪፖርቶች ውስጥ በዘመነ ቀይ ሽብር ይፈጸሙ የነበሩ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ሁሉ ዛሬም በዘመነ ወያኔ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ እየተፈጸሙ እንደሆኑ እናያለን። ከእነዚህ መሀል በድብደባ ብዛት ህይወታቸው ያለፈ ታሳሪዎች፣ ብልታቸው ላይ የውሃ ጠርሙስ የሚንጠለጠልባቸው ወንድ እስረኞች፣ በዱላ ብዛት ጽንስ የሚያስወርዱ ሴቶች፣ ለተከታታይ ቀናት እንዲቆሙ የሚገደዱ አዛውንቶችና የውሃ በርሜል ውስጥ የሚደፈቁ ተናዛዦች ይገኙበታል።

 

ለአብነቱ ያህል ተዛማጅነት ካላቸው ሌሎች ሶስት ኬብሎች መሀል ጥቂቶቹን ብቻ ነቅሰንና ጨምቀን እንደሚከተለው እንቃኛለን።

 

በሶማሌ ክልል የቀድሞው የኡጋዴኒ ጎሳ አለቃ የነበረው ሀሰን አህመድ ማክታል ደገሀቡር ውስጥ የታሰረው በኤፕሪል 2007 ዓ.ም ነበር። ወዲያውም ወደ ጅጅጋ እስር ቤት ተዛውሮ ከሁለት አመታት በላይ ዘብጥያ ቆየ። ሀሰን በዚህ ሁሉ እስር ጊዜው አንድም ጊዜ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ሲሆን ምንም አይነት ህጋዊ ክስም አልተመሰረተበትም።

 

ይህ ሰው በእስር ቆይታው የጤና መቃወስ የደረሰበት ቢሆንም ለ18 ወራት ያህል ያቀረበው የህክምና እርዳታ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም። የኋላ ኋላ ግን ሞት አፋፍ ላይ በመድረሱ ብቻ አሳሪዎቹ ሊለቁት መርጠዋል።

 

የዚህን ሰው ስቆቃ የመረመረው የኤምባሲው የፖለቲካ ኦፊሰር ኦክቶበር 26 ቀን ሀሰንን ሲያገኘው በእርግጥም በሞት አፋፍ ላይ ነበር።

 

“የፖለቲካ ኦፊሰራችን ሀሰንን ሲያገኘው መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፤ መናገርም አዳግቶታል። ክብደቱም 40 ኪሎግራም ደርሶ ነበር። ስለደረሰበት በደል የሰጠን ቃል በቅርቡ ካሰባሰብናቸው በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ከሚፈጸሙ በርካታ የሰብአዊ መብት ረገጣ ክሶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው።” ሲል የሮናልድ ያማማቶ ሪፖርት የክሱን ተአማኒነት ይደገፋል።

 

“እንደታሰርኩ” ይላል ሀሰን ለኤምባሲው ኢፊሰር የጭንቁን ወቅት ሲተርክ። “ፖሊስ ያሰርንህ አያትህ ማክታር ዳሂር በኡጋዴን ክልል በ1960ዎቹ ሁከት የቀሰቀሰ ሰው ስለነበር ነው አለኝ። በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገርፌያለሁ። እግሬ ተሰብሯል። የጎድን አጥንቴም ተጎድታል። ቆይቶም በሀይል ታመምኩ። ይሁንና እንደዚያ እየተሰቃየሁ እያዩ ለ18 ወራት ህክምና አልፈቀዱልኝም ነበር።

 

“በዚያ ላይ የእስር ቤቱ ሁኔታ እንኳን ለበሽተኛ ለጤነኛም ስቃይ ነበር። በአንዲት አራት ሜትር ተኩል በአራት ሜትር ተኩል በሆነች ክፍል ውስጥ ከሌሎች 200 እስረኞች ጋር ነበር የታጎርኩት። የምንተኛው አንዳችን በሌላችን ላይ ተደራርበን ነው።

 

“ከፍተኛ የውሃ ችግርም አለብን። በዚያ ሞቃት ሀገር የምንታጠብበት ስለሌለን የንጽህናው ሁኔታ አይጣል ነው። የምንጠጣው እንኳን ቆሻሻ ውሃ ነበር። መጸዳጃ ቤትም የለንም።

 

“በዚያ ላይ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እስረኞችን ማጉላላት ይወዳሉ። ከእኔ ጋር የታሰሩት አብዛኞቹ እስረኞች ፍርድ ቤት የሚባል ቀርበው አያውቁም።” ሲል የቀድሞው የጎሳ አለቃ ሀሰን አህመድ ማክታል በወያኔ እስር ቤት ያሳለፈውን ስቃይ ዘርዝሯል።

 

ይህ ሰው ከእስር ቤት ከተፈታ በኋላ ባደረገው የህክምና ምርመራ በሽታው ካንሰር ሆኖ መገኘቱንም የአምባሳደሩ ሪፖርት ጠቁሟል።

 

አምባሳደር ያማማቶ ይህንን ወደ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤታቸው ያስተላለፉትን ኬብል ሲያጠቃልሉ፦

 

“የሀሰን ምስክርነት በኛ እጅ ካሉ ሌሎች በርካታ ሪፖርቶች ጋር ተመሳሳይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የእስር ቤቶች መጨናነቅና የንጽህና ይዞታቸውን ልክ በተመለከተ የተወሰነ ማሻሻል ማድረጉ ቢነገርም ህገወጥ እስሩና የሰብአዊ መብት ረገጣው ግን ዛሬም ቀጥሏል።”

 

በመላው ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ዜጎችን ያለአንዳች ክስ ማሰርና አሰቃቂ ሰቆቃዎችን መፈጸም የእለት ተእለት ስሞታ ነው። አንዳንዴ ግን መንግስት በማናለብኝነት ያሰራቸውን ሰዎች ፍርድ ቤት ለማቅረብ ይፈልጋል። የሚለጥፍባቸው ክሶች መሰረት የለሽ በመሆናቸው የሚያቀርብባቸው መረጃዎች አይኖረውም። ስለዚህ ያለው አማራጭ እስረኞቹ እንዲናዘዙ ማድረግ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 27 መሰረት አንድ ተከሳሽ ወንጀሉን ሰርቻለሁ ብሎ የእምነት ቃሉን እስከሰጠ ድረስ መረጃ ባይቀርብበትም እንኳን ተጠያቂ ይሆናል። እናም የወያኔ መርማሪዎች ያሻቸውን ሰው ባሻቸው ወንጀል ስር እንዲናዘዝ የሚያደርጉበት ስልት አላቸው። አስቲ እንደናሙና ከሌላ የኢምባሲው ሪፖርት ላይ ጥቂት ምስክርነቶች እንይ፦

 

የ2005 ዓ.ምህረቱን ምርጫ ተከትሎ ሁከት አስነስታችኋል በሚል የታሰሩ 2 የፖለቲካ እስረኞች በአዲስ አበባ ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ለ3 ወራት ያህል የተፈጸመባቸውን ሰቆቃ ላናግራቸው የኢምባሲው የፖለቲካ ኦፊሰር በዝርዝር አስረድተዋል።

 

“ፖሊስ በሚፈልገው መንገድ ወንጀል ሰርተናል ብለው እንዲናዘዙ ለማስገደድ የተለያዩ የማሰቃያ ስልቶችን እንደተጠቀመባቸው ነግረውናል።” ይላል ሪፖርቱ መግቢያውን ሲጀምር፦

“እስረኞቹ እጅና እግራቸው በሰንሰለት ከመታሰር ጀምሮ ግርፊያም ተፈጽሞባቸዋል። ፖሊስ የውሃ ጠርሙስ ብልታቸው ላይ አንጠልጥሎ እንዳሰቃያቸውም ይናገራሉ። ምግብ በየሁለት ቀናቱ አንዴ ብቻ ነበር የሚሰጣቸው። ገላ መታጠብም ሆነ ልብሳቸውንም መቀየርም ተከልክለዋል።

 

“እነዚህ ሰዎች አብረዋቸው ከነበሩት እስረኞች መሀል ጸጋዬ አየለ ይግዛው፣ ገድሉ አየለ ሁሉአንተ እና አርጋታ ጎበና ማሩ የተባሉ ሶስት ታሳሪዎች በተደረገባቸው ከፍተኛ ድብደባና ህክምና በመነፈጋቸው ጦስ ህይወታቸው እንዳለፈ ምስክርነታቸውን ሰጥተውናል።

 

“አንዲት ውቢት ሌንጋሞ የተባለች ርጉዝ ሴትም ክፉኛ በመደብደቧ ጽንሷን እንዳስወረዳት ነግረውናል።” ይላሉ አምባሳደር ያማማቶ በሪፖርታቸው።

 

“አንድ በቅርቡ በዋስ የተፈታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባልም ታሳሪዎች በተለይም ወጣቶቹ እስረኞች ላይ ከፍተኛ ድብደባ የሚፈጸምባቸው ሲሆን ህክምና ግን እንደማይፈቀድላቸው ነግሮናል። እሱን ጨምሮ ሽማግሌዎቹን እስረኞች ግን ለረዥም ሰዓት እንዲቆሙ መደረጋቸውንም እንደምሳሌ ጠቅሶልናል።” ብለዋል።

 

በዚሁ ሪፖርት ላይ ያለአንዳች ክስ ለብዙ አመታት ስለታሰሩ ሰዎች አንድ ታስሮ የተፈታ እንግሊዛዊን ጨምሮ የተለያዩ ሰዎች ለኢምባሲው መመስከራቸው ተዘርዝራል። ዳኝነት ካገኙት ሰዎች መሀልም ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብታቸውም ፖሊስ አስሮ የሚያስቀራቸው በርካታ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመልክቷል።

 

ከኤምባሲው የተላለፈ አንድ ሌላ ኬብል ደግሞ በእውቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች በፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም ይመራ የነበረውና አለም አቀፍ ከበሬታ ያተረፈውን ኢሰመጉን ለማዳከም መንግስት ጠፍጥፎ የፈጠረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሳይቀር ለመናዘዝ የተገደደበትን አንድ ሪፖርት ያጣቅሳል።

 

ይህ በአምባሳደር ካሳ ገ/ህይወት የሚመራው አካል ራሱን ገለልተኛ ብሎ ቢጠራም እንኳን ህዝቡ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ሁሉ ኢህአዴግ ሰራሽ  አካል ስለመሆኑ የአሜሪካ ኢምባሲም ይተቸዋል።

 

ያም ሆኖ ግን ይህ መንግስታዊ ግፎችን ዓይን አውጥቶ ሲክድ የኖረ ተቋም ሳይቀር በዲሴምበር 2008 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርቱ ላይ የእስረኞች አያያዝ አስከፊ ስለመሆኑ፦ ግርፋትና እንግልት ይፈጸምብናል የሚሉ ክሶች ስለመኖራቸውና አብዛኞቹ እስረኞች ፍርድ ያላገኙ ስለመሆናቸው አትቷል።

 

በአስረጅነትም በጋምቤላ እስር ቤት ካሉት እስረኞች መሀል የተፈረደባቸው 10 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሷል።

 

በፌደራሉ 1ኛ ችሎት በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ ከቀረቡ 45ሺህ የወንጀል ክሶች መሀከልም 65 በመቶው ተከሳሾቹ በእስር ከቆዩ በኋላ በመረጃ እጦት ውድቅ የተደረጉ መሆናቸው ተነስቷል።

ይሁንና ይህ ኮሚሽን ለመንግስት የቆመ በመሆኑ የሚያውቀውን ያህል እንዳልመሰከረ አምባሳደር ያማማቶ ያሳደሩትን ግንዛቤ እንደሚከተለው እንመልከት፦

 

“የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በመንግስት የሚፈጸሙ ግፎችን በመሸፋፈን፣ በማጣጣልና ጭራሽም እንዳላየ ሆኖ በማለፍ የከፋ ስም ያተረፈ እንደመሆኑ ይህንን ሪፖርቱንም በተመለከተ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጸመውን መንግስታዊ በደል ያቀረበው አሳንሶ ብቻ እንደሆነ ማሰቡ ተገቢ ነው።” ይላሉ ያማማቶ። (በሚቀጥለው ክፍል በሌላ ርእሰ ጉዳይ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት)

You may also like...

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *